በግንባታ ስራዎች የሚታዩ ችግሮችን መፍታት ላይ ትኩረት ያደረገ የአንድ ወር የምክክር መድረክ በአራት ከተሞች ይካሄዳል - ኢዜአ አማርኛ
በግንባታ ስራዎች የሚታዩ ችግሮችን መፍታት ላይ ትኩረት ያደረገ የአንድ ወር የምክክር መድረክ በአራት ከተሞች ይካሄዳል
የካቲት 18 ቀን 2014 (ኢዜአ) በግንባታ ስራዎች የሚታዩ ችግሮችን መፍታት ላይ ትኩረት ያደረገ የአንድ ወር የምክክር መድረክ በአራት ከተሞች እንደሚካሄድ የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ባለሥልጣን አስታወቀ፡፡
የባለሥልጣኑ ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ማተቤ አዲስ ዛሬ በሰጡት መግለጫ እንዳሉት፤ የምክክር መድረኩ ከየካቲት 21 ጀምሮ "ግንባታ ለአገር አለኝታ" በሚል መሪ ሀሳብ ይካሄዳል፡፡
የኮንስትራክሽን ዘርፉ እያደገ ቢሆንም በርካታ ችግሮች እንዳሉበት ገልጸው፤ ችግሩን ለመፍታት በዋናነት ከባለድርሻ አካላት ጋር ተቀናጅቶ መሥራት ያስፈልጋል ነው ያሉት።
በመሆኑም የፌዴራልና የክልል ከተሞችን ያካተተና ባለድርሻ አካላት የሚሳተፉበት የውይይት መድረክ በአራት ከተሞች ለአንድ ወር እንደሚዘጋጅ ገልፀዋል።
የመጀመሪያው የምክክር መድረክ በድሬዳዋ ከተማ የሚከናወን ሲሆን፤ በመቀጠል በአዳማ ፣ ሐዋሳ እና ደሴ ከተሞች ይከናወናል ብለዋል።
በውይይት መድረኩ ላይ ሁሉም ክልሎችና በዘርፉ የሚሰሩ ባለድርሻ አካላት ተሳታፊ እንደሚሆኑ ይጠበቃል ነው ያሉት።
ለምክክር መድረኮቹ የሚሆኑ አራት የመወያያ ሰነዶች መዘጋጀታቸውን ገልጸው፤ የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ባለሥልጣን የቁጥጥር ሂደትን የሚመለከት ሰነድ የመጀመሪያው የመወያያ ጉዳይ እንደሚሆን ተናግረዋል፡፡
ከአራቱ መድረኮች የሚገኘውን ውጤት ክልሎች ወደ ራሳቸው ወስደው ይተገብሩታል ተብሎ እንደሚጠበቅም ጠቁመዋል።