ቀጥታ፡

ቱርክ በኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላም ለማስፈን የሚካሄደውን አገራዊ ምክክር በአውንታ ትመለከተዋለች

የካቲት 18 ቀን 2014 (ኢዜአ) "ቱርክ በኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላም ለማስፈን የሚካሄደውን አገራዊ ምክክር በአውንታ ትመለከተዋለች" ሲሉ በኢትዮጵያ የቱርክ አምባሳደር ያፍራቅ አልፍ ገለጹ፡፡

በኢትዮጵያ የቱርክ አምባሳደር ያፍራቅ አልፍ ለኢዜአ እንዳሉት፤ ኢትዮጵያና ቱርክ ለረጅም ዘመናትን ያስቆጠረ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት አላቸው፡፡

ሁለቱ አገራት ችግር በሚገጥማቸው ወቅትም እርስ በርስ በመደጋገፍ  አሳልፈዋል ነው ያሉት፡፡

ሁለቱ አገራት በፖሊቲካ፣ ኢኮኖሚ እንዲሁም በበርካታ ዘርፎች በትብብር እየሰሩ መሆኑንም ነው የገለጹት፡፡

በቅርቡ በርካታ የቱርክ ኤጀንሲዎችና መንግስታዊ ያልሆኑ ተቋማት በተለያዩ የኢትዮጵያ አካባቢዎች  የውሃ ፕሮጀክቶችን ከመገንባት ባሻገር የምርጥ ዘር ድጋፍ ማድረጋቸውንም ነው የተናገሩት፡፡

በቀጣይ የቱርክና ኢትዮጵያ ትብብር ይበልጥ እንደሚጠናከርም ያላቸውን እምነት ገልጸዋል፡፡

ቱርክ በኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላም ለማስፈን የሚካሄደውን አገራዊ ምክክር በአውንታ እንደምትመለከተው ጠቅሰው፤ ኢትዮጵያ ችግሮቿን በሰላም ለመፍታት የምታደርገው ጥረት አድንቀዋል፡፡

አገራዊ ምክክሩ  ዘላቂ ሰላም ለማስፈን ሚናው የጎላ መሆኑንም አብራርተዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ እንደአውሮፓዊያን አቆጣጠር በነሃሴ 2021 በቱርክ ይፋዊ ጉብኝት ባደረጉበት ወቅት አገራቱ በውሃ ሃብት ልማትና ወታደራዊ መስክ በትብብር ለመስራት የመግባቢያ ስምምነት መፈራረማቸው ይታወቃል፡፡

ኢትዮጵያና ቱርክ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት የጀመሩት እንደአውሮፓዊያን አቆጣጠር 1896 መሆኑን የታሪክ ድርሳናት ያመለክታሉ፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም