ቀጥታ፡

በሳዑዲ አረቢያ በእስር ላይ የሚገኙ ዜጎችን በአጭር ጊዜ ለመመለስ እየተሠራ ነው-አምባሳደር ሌንጮ ባቲ

የካቲት 18 ቀን 2014 (ኢዜአ) በሳዑዲ አረቢያ በእስር ላይ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ዜጎችን በአጭር ጊዜ ውስጥ ወደ አገራቸው ለመመለስ ከአገሪቱ መንግሥት ጋር በቅርበት እየተሠራ መሆኑን በሳዑዲ አረቢያ የኢትዮጵያ ኤምባሲ አስታወቀ።

በሳዑዲ አረቢያ የኢትዮጵያ ባለሙሉ ስልጣን አምባሳደር ሌንጮ ባቲ ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት በሰጡት አስተያየት፤ በተለያየ ምክንያት በሕገ ወጥ መንገድ ወደ ሳዑዲ አረቢያ ገብተው ለእስርና ለእንግልት የተዳረጉ ኢትዮጵያውያንን በአጭር ጊዜ ውስጥ ወደ አገራቸው ለመመለስ የኢትዮጵያ መንግሥት ከሳዑዲ አረቢያ መንግሥት ጋር በቅርበት እየሠራ ነው።

ከሳዑዲ የሚመለሱ ዜጎችን በተመለከተ ከተመለሱ በኋላ ችግር ላይ እንዳይወድቁ በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ የሚመራ ኮሚቴ ተቋቁሞ ከክልሎች ጋር ወደ ሥራ ተገብቷል ብለዋል።

በእሳቸው የሚመራው በሳዑዲ የሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ ሠራተኞችን ያካተተው ኮሚቴም በጉዳዩ ዙሪያ ከሳዑዲ አረቢያ መንግሥት ጋር በቅርበት እየሠራ መሆኑን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያና የሳዑዲ አረቢያ ግንኙነት ረጅም ዓመታትን ያስቆጠረ ግንኙነት በመሆኑ ኢትዮጵያውያን ከጥንት ጀምሮ ለሃይማኖታዊ እንቅስቃሴ፣ ለትምህርትና በሥራ ምክንያት ወደ ሳዑዲ አረቢያ ጉዞ ሲያደርጉ መቆየታቸውን ያወሱት አምባሳደሩ፤አሁንም በሳዑዲ አረቢያ ለእስራትና ለእንግልት የተዳረጉ ኢትዮጵያውያን ለተመሳሳይ ዓላማ ከአዲስ አበባ እስከ ሳዑዲና የመን ድረስ ኔትወርክ በዘረጉ ደላላዎች ተታልለው በህገ ወጥ መንገድ ወደ አገሪቱ እየገቡ መሆናቸውን ጠቁመዋል።

ለዜጎቻችን እስራት መነሻ የሆነው በንጉስ ሳልማን ቢን አብደልአዚዝ የሚመራው አዲሱ የሳዑዲ አረቢያ መንግሥት አገሪቱን ለማዘመን ብሎም በርካታ የሥራ ዘርፎች በሳዑዲ ዜጎች እንዲሸፈን አዲስ ራዕይ ይዘው መምጣታቸው ነው ያሉት አምባሳደሩ፤ ከሌሎች አገራት ወደ ሳዑዲ አረቢያ የሚሄዱ ሠራተኞች በሕግ አግባብ በተሟላ ሰነድ ብቻ በአገሪቱ መሥራት አለባቸው የሚል ገደብ በመቀመጡ ምክንያት መሆኑን ጠቅሰዋል።

በኢትዮጵያ የሰሜኑ ክፍል የተከሰተው ጦርነት ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጉዳት ቢያስከትልም የኢትዮጵያ መንግሥት በብዙ ውጥረት ውስጥ ሆኖ ከሳዑዲ መንግሥት ጋር በመነጋገር እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ 42 ሺ የሚጠጉ ዜጎችን ወደ አገር ቤት መመለሱን አምባሳደሩ አስታውሰዋል።

በአሁኑ ወቅትም ዜጎቻችን ወደ አገራቸው እስኪመለሱ ድረስ የሳዑዲ መንግሥት የዓለም አቀፉን የእስረኞች አያያዝ መብትን በማክበር በእስር ቤት ቆይታቸው አስፈላጊው ድጋፍ እንዲደረግላቸው ኤምባሲው በቅርበት እየተከታተለ መሆኑንም ገልጸዋል።

በሕጋዊ መንገድ ወደ ሳዑዲ ለመሄድ ተመዝግበው ነገር ግን የተፈጠረውን ችግር ፈርተው የቀሩ ወገኖችም መሄድ እንደሚችሉ አምባሳደር ሌንጮ ጠቁመዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ከሰሞኑ በጉዳዩ ላይ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በሰጡት ማብራሪያ፤ በሳዑዲ አረቢያ በእስር ላይ የሚገኙ ዜጎችን ወደ አገር ቤት ለመመለስ ማነቆ የሆነው አንዳንድ ዜጎች ፓስፖርት የሌላቸው፣ አንዳንዶቹ ደግሞ ኢትዮጵያዊ መሆናቸውን ማረጋገጥ አለመቻሉን ያለመሆን አለፍ ሲልም የሰለጠኑ ገዳዮች ከዜጎች ጋር ተቀላቅለው እንዳይገቡ ጥርጣሬ መኖሩን ጠቅሰው፤ ኢትዮጵያውያንን ግን ወደ አገራቸው ለመመለስ በመንግሥት በኩል ከፍተኛ ጥረት እየተደረገ መሆኑን አብራርተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም