የሕዳሴ ግድብ ለብርሃን መብቃቱ ድል ከተበሰረ በኋላም የአገር ወዳዶች ድጋፍ በይበልጥ ተጠናክሮ ቀጥሏል - ኢዜአ አማርኛ
የሕዳሴ ግድብ ለብርሃን መብቃቱ ድል ከተበሰረ በኋላም የአገር ወዳዶች ድጋፍ በይበልጥ ተጠናክሮ ቀጥሏል
አዲስ አበባ የካቲት 17/2014/(ኢዜአ) የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ለብርሃን መብቃቱ ድል ከተበሰረ በኋላም የአገር ወዳዶችን የድጋፍ ወኔ ይበልጥ እንዳነሳሳቸው ለግድቡ ድጋፍ አድራጊዎች ተናገሩ።
የኢትዮጵያዊያን የሰንደቅ ዓላማ ፕሮጀክት የሚሰኘው ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ከሰሞኑ የመጀመሪያ ዙር ኃይል ማመንጨቱ መበሰሩ ይታወሳል።
ኢትዮጵያዊያን ለዚህ ግድብ ፕሮጀክት ዕውን መሆን ከመቀነት ገንዘባቸው እስከ መኖሪያ ቤታቸው፣ ከልጅ ልደት ወጪያቸው እስከ ጣት ቀለበታቸው፣ ከቦንድ ግዥ እስከ ዓይነት ድጋፍ አሻራቸውን አሳርፈዋል።
ግድቡ መልከ ብዙ ጫናዎችን ተሻግሮ ለብርሃን የመብቃቱ ድል ከተበሰረ በኋላም ቀድሞውኑም ድጋፉ ልኩ ከፍታ የነበረው ይህ ፕሮጀክት የአገር ወዳዶችን የድጋፍ ወኔ ይበልጥ ቀስቅሷል።
ቀደም ሲል መኖሪያ ቤታቸውን በመሸጥ ሳይቀር በሕልውና ዘመቻው ተጋድሎ ላደረጉ መከላከያ ሰራዊት አባላት፣ በጦርነቱ ለተጎዱ ወገኖች፣ ለልማት ፕሮጀክቶች ገንዘባቸውን ሳይሰስቱ የለገሱት ወይዘሮ ቦጋለች ከበደ ለዚህ አብነት ናቸው።
ወይዘሮ ቦጋለች የኢትዮጵያን ተስፋ ያለመለመውና የትውልድ ዓርማ የሆነው የሕዳሴ ግድብ ፕሮጀክት ሃይል ማመንጨቱን ተከትሎ በዛሬው ዕለት የአንድ ሚሊየን ብር ስጦታ በማድረግ ደስታቸውን ገልጸዋል።
የገንዘብ ድጋፉንም በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ማስተባበሪያ ፕሮጀክት ፅህፈት ቤት ተገኝተው ለጽህፈት ቤት ቤቱ ዋና ዳይሬክተር ዶክተር አረጋዊ በርሔ አስረክበዋል።
በተመሳሳይ ቫሞስ ኢንተርቴመንት ሃላፊነቱ የተወሰነ የግል ድርጅትም እንደ ወይዘሮ ቦጋለች ሁሉ የአንድ ሚሊየን ብር ስጦታ በማድረግ በዓባይ ወንዝ ላይ በፈነጠቀው ብርሃን ደስታውን ገልጿል።
የድርጅቱ ስራ እስኪያጅ የኔብለህ ባንታየሁ እና ወይዘሮ ቦጋለች ከበደ እንዳሉት ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ብዙ ውጣረዶችን አልፎ ለኤሌክትሪክ ብርሃን መብቃቱ እንዳስደሰታቸው ተናግረዋል።
ለግድቡ ሲያደርጉት የነበረውን ድጋፍ ወደፊትም አጠናክረው እንደሚቀጥሉ አረጋግጠዋል።
የግድቡ አንድ ተርባይን ሃይል ማመንጨት ብስራት የኢትዮጵያውያዊያንን ተስፋን ያለመለመ ድል እንደሆነም ገልጸዋል።
ግድቡ ለመጭው ትውልድ የሚተርፍና አገርን ከድህነት አረንቋ የሚያላቅቅ በመሆኑ የግድቡ ግንባታ ተጠናቆ ወደ ሙሉ ሃይል ማመንጨት አቅሙ እስኪገባ ድጋፉ ሊጠናከር ይገባል ነው ያሉት።
የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ህዝባዊ ተሳትፎ ማስተባበሪያ ብሄራዊ ምክር ቤት ፅህፈት ቤት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር አረጋዊ በርሄ ድጋፍ አድራጊዎችን አመሰግነው፤ የግድቡ አንድ ዩኒት ሃይል ማመንጨቱ ትልቅ የድል ምዕራፍ ነው ብለዋል።
ኢትዮጵያዊያን ካለማንም ድጋፍ በራሳቸው አቅምና ጉልበት የገነቡት ፕሮጀክት በመሆኑ የግድቡ ኃይል ማመንጨት መጀመር አንድምታው ከፍተኛ እንደሆነ ነው ያነሱት።
ኢትዮጵያዊያን በአንድነትና በትብብር ጥረት ካደረጉ ከድህነት መውጣት እንደሚቻል ማሳያ ስለመሆኑ ጠቅሰዋል።
ኢትዮጵያዊያን ለግድቡ መጨረሻ ዕውን መሆን ሲያደርጉት የነበረውን አስተዋጽኦ እንዲያጠናክሩም ጥሪ አቅርበዋል።
ግድቡ ካሉት 13 ተርባይኖች መካከል አንዱ የካቲት 13 ቀን 2014 ዓ.ም 375 ሜጋ ዋት ኃይል ማመንጨት መጀመሩ ይታወቃል።