ቀጥታ፡

የሚኒስትሮች ምክር ቤት የተለያዩ ጉዳዮች ላይ ውሳኔ አሳለፈ

አዲስ አበባ ነሃሴ 26/2010 የሚኒስትሮች ምክር ቤት በዛሬው ዕለት ባካሄደው 53ኛ መደበኛ ስብስባ በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ተወያይቶ ውሳኔ ማሳለፉን የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ለኢዜአ በላከው መግለጫ አመልክቷል። ምክር ቤቱ የኢትዮጵያ ዲያስፖራ ኤጀንሲን ለማቋቋም በቀረበው ረቂቅ ደንብ፣ ብሔራዊ የሎጂስቲክስ ስትራቴጂና በመንግስት ግዙፍ የልማት ድርጅቶች ውስጥ ያለውን ድርሻ በከፊል ወደ ግል ለማዛወር የተላለፈውን ውሳኔ ለማስፈጸም በተዘጋጀው ጋይድ ላይን ላይ  መክሮ ውሳኔ አሳልፏል። የኢትዮጵያ ዲያስፖራ ኤጀንሲ መቋቋም መንግስት በውጭ ያሉ ኢትዮጵያዊያን እና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን በአገራቸው ሁለንተናዊ  እድገት ላይ የሚኖራቸውን ገንቢ አስተዋዕኦ መሰረት በማድረግ ሁሉም የዳያስፖራ አባላት በአገር ልማት ላይ የጋራ አቋም እንዲይዙ ለማስቻልና በመንግስት የተቀመጠውን የፖሊሲ አቅጣጫ ለማስፈጸም ይረዳል ተብሏል። በመሆኑም የቀረበው ረቂቅ ደንብ ውይይት ከተደረገበት በኋላ አንዳንድ ማሻሻያዎችን በማከል በነጋሪት ጋዜጣ ታትሞ እንዲወጣና በስራ ላይ እንዲውል ምክር ቤቱ ወስኗል። ብሔራዊ የሎጂስቲክስ ስትራቴጂ ላይ የመከረው ምክር ቤቱ ላለፉት አስር ተከታታይ ዓመታት የተመዘገበው አጠቃላይ የኢኮኖሚ እድገትን ተከትሎ የገቢና የወጭ እቃዎችና የአገር ውስጥ የንግድ እንቅስቃሴ በመጠንና በአይነት በከፍተኛ ፍጥነት በማደግ ላይ እንደሆነ ተመልክቷል። በመሆኑም በአገራችን የውጭ ንግድ ልማትን ለመደገፍ መከናወን ካለባቸው ቁልፍ ተግባራት ውስጥ ዋናው ቀልጣፋና ውጤታማ የሎጂስቲክስ ስርዓት ለመዘርጋት ብሔራዊ የሎጂስቲክስ ስትራቴጂ በስራ ላይ አንዲውል ምክር ቤቱ ወስኗል። ምክር ቤቱ በመጨረሻም በመንግስት ግዙፍ የልማት ድርጅቶች ውስጥ ያለውን ድርሻ በከፊል ወደ ግል ለማዛወር የተላለፈውን ውሳኔ ለማስፈጸም በተዘጋጀው ጋይድ ላይን ላይ ተወያይቶ ውሳኔ አሳልፏል። ምክር ቤቱ የተወያየበት የፕራይቬታይዜሽን ፕሮግራሙ የሚመራበትን የአሰራር ስርዓት የሚያመለክት ጋይድ ላይን በስራ ላይ እንዲውል ወስኗል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም