ቀጥታ፡

የጠቅላይ ሚኒስትሩ ማብራሪያ የነበረብንን ብዥታ ያጠራ ነው - የጎባ ከተማ ነዋሪዎች

ጎባ ፤ የካቲት 17/2014(ኢዜአ) ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ ከህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች የሰጡት ማብራሪያና ምላሽ አግባብነት ያላቸውና ብዥታቸውን ያጠራ መሆኑን የጎባ ከተማ ነዋሪዎች ገለጹ፡፡

ማብራሪያውን በማስመልከት ኢዜአ ካነጋገራቸው  የጎባ ከተማ ነዋሪዎች መካከል አቶ አብዱልፈታህ ኡመር፤ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በብልሹ አሰራርና በዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ላይ የሰጡት ማብራሪያ የነበረባቸውን ብዥታ እንዳጠራላቸው ተናግረዋል፡፡

በተለይም በኢኮኖሚ ዕድገት፣ በዲፕሎማሲ፣ በሀገራዊ   ምክክርና በመንግስት መስሪያ ቤቶች ውስጥ በሚስተዋሉ ብልሹ አሰራሮች ላይ የሰጡት ማብራሪያ የመንግስትን ቁርጠኝነት ያሳዩበት ነው ብለዋል።

ሌላው የከተማዋ ነዋሪ ጀማል ከድር እንዳሉት፤ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሴክተር መስሪያ ቤቶች አካባቢ የሚስተዋሉ ብልሹ አሰራሮችና ሌብነትን ለማስተካከል ቀጣይነት ያለው ግምገማ እያካሄዱ መሆናቸውን ግልጽ አድርገዋል፡፡

ይህም መንግስታቸው ለችግሩ እልባት ለማስገኘት የሰጠውን ትኩረት እንደሚያመለክት መረዳታቸውን  ገልጸዋል።

ህዝቡ የመንግስትን አገልግሎት በአግባቡ እንዳያገኝና የመልካም አስተዳደር ችግሮች እንዲፈጠሩ በሚያደርጉ ሰራተኞችና አመራሮች ላይ እስከ ታችኛው እርከን ድረስ በመፈተሸ የማስተካከያ እርምጃ ሊወሰድ እንደሚገባም ጠቁመዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ኃይል ማመንጨት መጀመሩንና ሌሎች ተያያዥ ጉዳዮች ዙሪያ የሰጡት ማብራሪያ የኢትዮጵያን የማይዋዥቅ አቋምና ሀቅን የሚያሳይ ነው ያሉት ደግሞ ሌላኛው አስተያየት ሰጪ አቶ መሐመድ አማን ናቸው።  

ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ሃይል በማመንጨት ጉዞውን መቀጠሉ በግድቡ ላይ ግትር አቋም ለነበራቸው ሀገራት ጭምር  ብዥታን የሚያጠራ እውነት እንደሆነ መገንዘባቸውን ተናግረዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሀገራዊ ምክክሩ  ኮሚሽነሮች  ሹመት ላይ የሰጡት ማብራሪያም ይነዛ የነበረውን አሉባልታ ያጠራ፣ የኮሚሽነሮችን ዓላማና የስልጣን ደረጃን ጭምር ግልጽ ያደረገ መሆኑን  አስተያየት ሰጪዎቹ አመላክተዋል።

የሀገር ሰላምና አንድነትን በማስጠበቅ ተስፋ ያላት ኢትዮጵያን  ለመገንባት እንዲያግዝ የሚካሄደው ሀገራዊ ምክክር  የሚፈለገውን ዓላማ እንዲያሳካም ሁሉም ዜጋ ሊተባበር እንደሚገባም ጠቁመዋል።

አስተያየት ሰጪዎቹ ፤ጠቅላይ ሚኒስትሩ በተለይም 'አምስቱ-ዲ'ዎች  ብለው የዘረዘሯቸው መከላከያ፣ ሀገራዊ ምክክር፣ ዓለም አቀፍ ግንኙነት፣ ልማትና ዴሞክራሲ ዙሪያ የሰጡት ማብራሪያ   የመንግስትን ቀጣይ አቅጣጫ ጭምር ያሳየና ለተግባራዊነቱም የድርሻቸውን እንደሚወጡ ነው የገለጹት።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም