ቀጥታ፡

ማህበሩ ለተፈናቃዮች 3 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት ድጋፍ አደረገ

ደብረ ብርሃን የካቲት 17/2014(ኢዜአ) የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበር በአሸባሪው ሸኔ ቡድን ተፈናቅለው በደብረ ብርሃን ጊዜያዊ መጠለያ ጣቢያ ለሚገኙ ወገኖች 3 ነጥብ 6 ሚሊዮን ብር የሚገመት ድጋፍ አደረገ።
የማህበሩ የሰሜን ሸዋ ዞን ቅርጫፍ ጽህፈት ቤት ሀላፊ አቶ ዳምጠው እምሻው ድጋፉን ለሰሜን ሸዋ ዞን አደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ተጠሪ ጽህፈት ቤት አስረክበዋል።

ድጋፉ 200 ኩንታል የዳቦ ዱቄት፣ መኮሮኒ፣ፓስታ፣ ሩዝ፣ 2 ቦንዳ ብርድ ልብስ፣ አልባሳት፤ ጫማዎች፣ የንጽህና መጠበቂያዎችን እንዳካተተ አስታውቀዋል።

ማህበሩም ማህበራዊ ሃላፊነት ለመወጣት በጦርነት ተፈናቀሉ ወገኖችን  ለማገዝ  እያደረገ ያለውን ጥረት አጠናክሮ  እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።

በግጭቶች ውስጥ በሰላማዊ ዜጎች ላይ የሚደርሰው ጉዳት የከፋ መሆኑን አመልክተው፤ በተለይም ከመኖሪያ ቀያቸው ለተፈናቀሉ ወገኖችን ለመርዳት ፈጥኖ መድረስ ይገባል ብለዋል።

በአማራ ክልል የሰሜን ሸዋ ዞን  አደጋ መከላከልና  ምግብ ዋስትና  ተጠሪ ጽህፈት  ቤት ሃላፊ አቶ አበባው መሰለ በዞኑ በ12 ወረዳዎች የዕለት ድጋፍ የሚሹ ከ46 ሺህ በላይ ተፈናቃዮች እንደሚገኙ አስታውቀዋል።

ከዚህ ውስጥ 19 ሺህ 200 ያህሉ በደብረ ብርሃን ከተማ  በጊዜያዊ  መጠለያ  ጣቢያዎች  እንደሚገኙ ገልጸው፤ ቀሪዎቹ በግለሰብ ቤቶች ተጠግተው የሚገኙ ናቸው ብዋል።

ማህበሩ ተፈነቃዮቹ ለከፋ ችግር እንዳይጋለጡ ላደረገው ድጋፍ አመስግነው፣ ሌሎች መንግሥታዊና መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችም ድጋፍ እንዲያደርጉ ጠይቀዋል።

''ከምዕራብ ሸዋ ዞን ዳኖ ወረዳ 57 ዓመት ከኖርኩበት ቀየ ተፈናቅዬ ለችግር ተዳርጊያለሁ'' ያሉት ደግሞ ወይዘሮ አስካለ ተረፈ ናቸው።

መንግሥታዊና መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች እንዲሁም የደብረ ብርሃን ከተማ  ህዝብ ድጋፍ  እያደረገላቸው  ቢሆንም፤  ሕይወታቸውን  በቀጣይ  ለመምራት  ግን ዘላቂ መፍትሄ እንደሚፈልጉ ገልጸዋል።

አቶ አድማሱ ማሞ የተባሉ የዚሁ ወረዳ ተፈናቃይ በበኩላቸው አሸባሪው ሸኔ  በፈጠረው ችግር ምክንያት ''ተወልጄ ባደግኩበት አካባቢ የመኸር አዝመራ ሳልሰበሰብ ተፈናቅዬ ተረጂ ሆኛለሁ'' ብለዋል።

መንግሥት ያፈናቀላቸው ቡድን ላይ እርምጃ በመውሰድ ወደ ቀደመ መኖሪያቸው እንዲመልሳቸውም ጠይቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም