ለስድስት ሀገር በቀል ምርቶች ደረጃ ተዘጋጅቷል -ኢንስቲትዩት - ኢዜአ አማርኛ
ለስድስት ሀገር በቀል ምርቶች ደረጃ ተዘጋጅቷል -ኢንስቲትዩት
አዳማ የካቲት 17/2014/ኢዜአ/---በሀገር ውስጥና በውጭ ገበያ ተፈላጊ ለሆኑ በርበሬ፣ ሽሮ፣ ቆሎና በሶን ጨምሮ ለስድስት ሀገር በቀል ምርቶች ደረጃ ማዘጋጀቱን የኢትዮጵያ ደረጃዎች እንስቲትዩት አስታወቀ።
ኢንስቲትዩቱ ደረጃ የተዘጋጀላቸው ሀገር በቀል ምርቶች ጥራታቸውን ጠብቀው እንዲዘጋጁ አምራቾች በተዘጋጀላቸው የደረጃ ማዕቀፎች ላይ ግንዛቤ እንዲኖራቸው ያለመ መድረክ በአዳማ ከተማ ተካሄዷል።
ለሀገር በቀል ምርቶች ዓለም አቀፋዊ የጥራት ደረጃ እንዲኖራቸው ለማስቻል ደረጃ መዘጋጀቱን የኢንስቲትዩቱ የኮሚዩኒኬሽንና የህዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር አቶ ይስማ ጅሩ ገልፀዋል።
በተለይ በሀገር ውስጥና በውጭ ጭምር ተፈላጊነታቸው እየጨመረ የመጣውን በርበሬ ሽሮ ፣ቆሎ፣በሶ፣ጠጅና አረቄ በጥናትና ምርምር የተደገፈ ደረጃዎች እንደተዘጋጀላቸው ተናግረዋል።
አምራቾች ደረጃዎችን ተጠቅመውና ማዕቀፉን ብቻ ጠብቀው ምርቶቹን በጥራት የማዘጋጀት ግዴታ እንዳለባቸው አመልክተዋል።
በተለይ የዘርፉ አምራች ኢንዱስትሪዎች፣ በጥቃቅንና አነስተኛ የተደራጁ ኢንተርፕራይዞች ደረጃ በተዘጋጀላቸው የሀገር በቀል ምርቶች የደረጃዎች ማዕቀፍ ጠብቀው እንዲያመርቱ ለማስቻል እየተሰራ መሆኑን ዳይሬክተሩ ተናግረዋል።
እጅጉን ተፈላጊ ለሆኑ የሀገር በቀል ምርቶች ደረጃዎች መውጣቱ የሻጭና አምራችን ፍላጎት ከሟሟላትና ደህንነታቸው ከመጠበቅ አንፃር ከፍተኛ ጠቀሜታ እንዳለው አመልክተዋል።
በተለይ ሽሮ፣ በርበሬ፣ ቆሎና በሶ ከሀገር ውስጥ ፍጆታነት ባለፈ ጣእማቸውን ጠብቀው በጥራት ተመርተው ተፈትሸው ወደ ዓለም ገበያ እንዲቀርቡና የውጭ ምንዛሬ ምንጭ ለማድረግ እንደሚቻልም ገልጸዋል።
በሀገሪቱ የኢኮኖሚ እድገት ውስጥ ጉልህ ሚና እንዲኖራቸውና ሰፊ የስራ እድል የሚፈጠርበት ዘርፍ ለማድረግ ጭምር እንደሆነም አቶ ይስማ ተናግረዋል።
ቡላና ቆጮን ጨምሮ ለበርካታ ሀገር በቀል ምርቶች ደረጃ ለማውጣት፣ ደህንነታቸውና ጣእማቸውን ለመፈተሽ የሚያስችል ቤተ-ሙከራ የማደራጀት ስራ በኢንስቲትዩቱ እየተከናወነ መሆኑን አመልክተዋል።
የአስቴር ጠጅ ቤት ባለቤት ወይዘሮ አስቴር ሰይፈ በበኩላቸው "ለጠጅና አረቄ ምርት ደረጃ መዘጋጀቱ በሀገር ውስጥ ገበያ ጥራት ያለው ምርት ለማቅረብና ምርቱን ወደ ውጭ ገበያ ተደራሽ ለማድረግ ወሳኝ ነው" ብለዋል።
"ጥራትና ደህንነቱ የተጠበቀ ምርት ለማዘጋጀት ደረጃ መውጣቱ ተወዳዳሪ ለመሆን ያስችለናል" ያሉት ደግሞ የማርቃን ቅመማ ቅመምና ባልትና ባለቤት ወይዘሮ ኤልሳቤት መስፍን ናቸው።