ቀጥታ፡

ትምህርት ቤቶች ለአዲሱ የትምህርት ዘመን ዝግጅት አድርገዋል

አዲስ አበባ ነሃሴ 26/2010 በአዲስ አበባ የሚገኙ የመንግስት ትምህርት ቤቶች ለ2011 የትምህርት ዘመን ዝግጅት ማጠናቀቃቸውን ገለጹ፡፡ በተለይም የኢዜአ ሪፖርተር ተዘዋውሮ የቃኛቸው የመንግስት ትምህርት ቤቶች ለአዲሱ የትምህርት ዘመን ዝግጅት ማጠናቀቃቸውን አስተውሏል፡፡ አንዳንድ ትምህርት ቤቶችም ለማማር ማስተማሩ የሚረዱ ቁሳቁሶች ግዥ እንዲሁም ጥገና እና እድሳት በማጠናቀቅ ላይ መሆናቸውን ተመልክተናል፡፡ ለኢዜአ አስተያየታቸውን የሰጡ ትምህርት ቤቶችም ለመማር ማስተማሩ የሚያግዙ የሰው ሃይል፣ የግብዓት እና ተያያዥ ተግባራትን ሲያከናውኑ መቆየታቸውን ጠቁመዋል፡፡ እንዲሁም የመማር ማስተማሩ ሂደት ሰላማዊ ሆኖ እንዲቀጥል በትኩረት እንደሚሰሩም ገልጸዋል፡፡ በተለይም ከመማሪያ ክፍሎች እድሳት፣ ከሰው ኃይል ቅጥር፣ ከትምህርት መርጃ መሳሪያዎች ማሟላት ጋር የተያያዙ ተግባራት በክረምቱ ወቅት ሲከናወን መቆየቱን ተናግረዋል። የየካቲት 12 መሰናዶ ትምህርት ቤት ርዕሰ-መምህር አቶ ደምረው አሰፋ እንዳሉት የመምህራን ልየታ ፣ በመማሪያ ግብዓቶችና የክፍሎች እድሳት እንዲሁም  ፕላዝማ በመስራት ላይ መሆኑን  የማረጋገጥ ስራ ተሰርቷል ብለዋል፡፡ የእየሩሳሌም የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት የመማር ማስተማር ምክትል ርዕሰ መምህር ተወካይ አቶ  ጌታቸው ደበበ በበኩላቸው  የ2011 እቅዶች ወጥተው እያንዳንዱ ሰራተኛ  የራሱን እቅድ አመጣጥኖ ማውጣቱን ተናግረዋል፤ እንዲሁም የክፍሎች ፅዳትና አዳዲስ መምህራንን የመደልደል ስራ መከናወኑን አስታውቀዋል፡፡ የዳግማዊ ምኒልክ መሰናዶ ትምህርት ቤት የአደረጃጀትና የትምህርት ፕሮግራሞች ምክትል ርዕሰ መምህር አቶ ኪዳነማርያም አረጋይ እንደገለፁት ትምህርት ቤቱን በማፅዳት ለመማር ማስተማር ዝግጁ ማድረግ  ፤የመጽሐፍት እደላና ላይብረሪውን ወደ ዲጅታል የማዘጋጀት ተግባራት  ሲሰሩ መቆየታቸውን ገልፀዋል፡፡ ርዕሳነ መምህራኑ   ትምህርት በሚጀመርበት ወቅት መምህራኑ በእቅድ እንዲመሩ የሚያስችሉ ተግባራት ቀደም ብለው መጠናቀቃቸውን ተናግረዋል፡፡ የመማር ማስተማሩ ሂደት ሰላማዊ እንዲሆን እንደሚሰራም ነው ርዕሳነ መምህራኑ የተናገሩት፡፡    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም