ሚኒስቴሩ በሶማሌ ክልል በድርቅ ለተጎዱ ዜጎች 5 ሚሊዮን ብር ግምት ያለው የምግብ ድጋፍ አደረገ - ኢዜአ አማርኛ
ሚኒስቴሩ በሶማሌ ክልል በድርቅ ለተጎዱ ዜጎች 5 ሚሊዮን ብር ግምት ያለው የምግብ ድጋፍ አደረገ
የካቲት 16/2014/ኢዜአ/ የውኃና ኢነርጂ ሚኒስቴር በሶማሌ ክልል በድርቅ ለተጎዱ ዜጎች 5 ሚሊዮን ብር ግምት ያለው የምግብ ድጋፍ አደረገ።
የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትር ዶክተር ኢንጅነር ኃብታሙ ኢተፋ ድጋፉን ለሶማሌ ክልል ርእሰ መስተዳደር ፅህፈት ቤት ኃላፊ ዶክተር ሁሴን ሀሺ ቃሲም አስረክበዋል።
ሚኒስትር ዶክተር ኢንጅነር ኃብታሙ በዚሁ ጊዜ እንደገለጹት፤ ሚኒስቴሩ በየጊዜው የሚከሰተውን ድርቅ ለመከላከል በዘላቂነት ለመከላከል ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ ነው።
በተለይም በዘላቂነት የውሃ ልማትን በማጠናከር በየጊዜው የሚከሰተውን ድርቅ ለመቋቋም የተለያዩ የልማት ሥራዎች በመካሄድ ላይ መሆናቸውን ነው የገለጹት።
አየር ንብረትን የሚቋቋም ፕሮጀክቶችን ተግባራዊ በማድረግ አርብቶ አደሩንና ደረቃማ አካባቢ የሚኖሩ ዜጎችን ተጠቃሚ የሚያደርጉ ሥራዎችም መኖራቸውን ተናግረዋል።
እነዚህና ሌሎች በመካሄድ ላይ የሚገኙ የውኃ ፕሮጀክት ግንባታዎችን በፍጥነት ለማጠናቀቅና ኅብረተሰቡን ተጠቃሚ ለማድረግ እንደሚሰራም ሚኒስትሩ አረጋግጠዋል።
ሚኒስቴሩ 5 ሚሊዮን ብር ግምት ያለው የምግብ ድጋፍ ማድረጉን ጠቁመው ይህም በክልሉ በድርቅ የተጎዱ ወገኖችን የእለት ደራሽ ምግብነት የሚውል መሆኑን ገልጸዋል።
የሶማሌ ክልል ርእሰ መስተዳደር ፅህፈት ቤት ኃላፊ ዶክተር ሁሴን ሐሺ ቃሲም፤ በሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ስለተደረገው ድጋፍ አመስግነዋል።
በክልሉ ድርቁ ያስከተለውን ችግር ለመሻገር ሌሎችም ተመሳሳይ ድጋፍ እንዲያደርጉ ጠይቀዋል።