በትግራይ ክልል በሙስና ወንጀል የተከሰሱ ሁለት ኃላፊዎች በገንዘብና በእስራት ተቀጡ - ኢዜአ አማርኛ
በትግራይ ክልል በሙስና ወንጀል የተከሰሱ ሁለት ኃላፊዎች በገንዘብና በእስራት ተቀጡ
መቀሌ ነሃሴ 26/2010 ስልጣንን መከታ በማድረግ የሙስና ወንጀል የፈጸሙ ሁለት የውቅሮ ከተማ ቤቶች ኤጀንሲ የሥራ ኃላፊዎች በእስራትና በገንዘብ እንዲቀጡ ማድረጉን የትግራይ ክልል ስነ-ምግባርና ጸረ-ሙስና ኮሚሽን አስታወቀ። ኮሚሽኑ ለኢዜአ በላከው መግለጫ እንዳመለከተው የስራ ሀላፊዎቹ የተቀጡት በከተማው የቤት ልማት ተጠቃሚ ለሆኑ 46 ባለእድሎች የወጣውን የጋራ መኖሪያ ቤት በሃሰት ሰነድ ለሌላ ሰው እንዲተላለፍ በማድረጋቸው ነው። የኤጀንሲው ኃላፊ ክፍሎም ሃፍቱና የቤቶች ማስተላለፍ ኃላፊ ዳርጌ መረሳ ባለ እጣዎቹ ቤቶቹን እንደማይፈልጉ ሲገልጹ በአሰራሩ መሰረት ከከፈሉት ተቀንሶ ለመንግስት ገቢ ማድረግ ሲገባቸው ቤቶቹን አየር በአየር ለሌሎች ሰዎች መሸጣቸው በማስረጃ መረጋገጡ ነው የተገለጸው፡፡ በዚህም መንግስት ማግኘት የሚገባውን 131ሺህ 916 ብር በማሳጣት ለግል ጥቅም በማዋላቸው ክስ እንደቀረበባቸው ኮሚሽኑ አስረድቷል። ክሱን ማስተባበል ባለመቻላቸው የውቅሮ ከፍተኛ ፍርድ ቤት የኤጀንሲው ኃላፊ ክፍሎም ሀፍቱ በ13 አመት ከስድስት ወር ጽኑ እስራትና 18ሺህ ብር እንዲሁም ሁለተኛው ተከሳሽ ዳርጌ መረሳ በሰባት አመት ጽኑ እስራትና በ10ሺህ ብር መቀጣታቸውን ኮሚሽኑ አስታውቋል።