ኢትዮጵያ የቀይ ባህር አዋሳኝ አገሮች ከፈጠሩት "የቀይ ባህር ፎረም" ውጭ መደረጓ በፍፁም ተገቢነት የለውም - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ የቀይ ባህር አዋሳኝ አገሮች ከፈጠሩት "የቀይ ባህር ፎረም" ውጭ መደረጓ በፍፁም ተገቢነት የለውም
የካቲት 17/2014/ኢዜአ/ ኢትዮጵያ የቀይ ባህር አዋሳኝ አገሮች ከፈጠሩት "የቀይ ባህር ፎረም" ውጭ መደረጓ በፍፁም ተገቢነት የሌለው መሆኑን ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ማስረዳት መቻሉን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ገለጸ፡፡
ለአፍሪካ ቀንድና የቀይ ባህር ቀጣና የሰላም እጦት የውጭ ጣልቃ ገብነት የተበላሸ ምርጫና ድንበር ተሻጋሪ ወንዞች ዋነኛ ምክንያቶች መሆናቸውም ተመልክቷል።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ፤ በፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚና ዜጋ ተኮር ዲፕሎማሲ ዙሪያ ሳምንታዊ መግለጫ ሰጥተዋል።
በመግለጫቸውም በስድስተኛው የአፍሪካ ህብረትና የአውሮፓ ህብረት የጋራ ስብሰባ ወቅት ከመደበኛው ስብሰባ ባሻገር በስምንተኛው የሙኒክ የደህንነት ኮንፈረስና በጣና ፎረም የነቃ ተሳትፎ ማድረጓን ገልጸዋል፡፡
ኢትዮጵያ በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን አማካኝነት በስምንተኛው የሙኒክ የደህንነት ኮንፈረንስ ላይ መሳተፏን ገልጸዋል፡፡
በኮንፈረንሱ ላይም የኮቪድ -19 ወረርሽኝ፣ ሙስና፣ በእውቀት ሽግግርና ሰላምና ደህንነት ላይ ያተኮረ ውጤታማ ውይይት አድርጋለች ብለዋል።
በአፍሪካ ቀንድና የቀይ ባህር ቀጣና ሽብርተኝነትን መከላከል፣ ሰላምና መረጋጋት መፍጠር በሚቻልባቸው ጉዳዮች ዙሪያ በጋራ መስራት እንደሚገባም ተነስቷል ብለዋል።
በአፍሪካ ቀንድና በቀይ ባህር ቀጣና የኢኮኖሚ ውህደትና ሰላማዊ ሁኔታ በመፍጠር ሽብርተኝነትን በጋራ ለመከላከል አለም አቀፍ ድጋፍና ትብብር ያስፈልጋል ብለዋል።
ይሁን እንጂ የቀይ ባህር አዋሳኝ አገሮች እንደ አውሮፓውያን የዘመን ቀመር በ2019 ከመሰረቱት "የቀይ ባህር ፎረም" ኢትዮጵያን ያገለለ መሆኑን ጠቅሰዋል።
ኢትዮጵያ የአፍሪካን ቀንድ በትራንስፖርት በማስተሳሰር የመሪነት ሚና መጫወት የሚያስችል አቅም እንዳላት እየታወቀ ከፎረሙ ውጭ መሆኗ ፍፁም ተገቢነት የለውም ነው ያሉት።
በአፍሪካ ቀንድና የቀይ ባህር ቀጣና ያለውን ህገ ወጥ የሰዎች ዝውውር መግታትና ሽብርተኝነትን ለመዋጋት በጋራ መስራት ይገባልም ብለዋል፡፡
ዘር ተኮር ግጭት፣ የውጭ ጣልቃ ገብነት፣ ድንበር ተሻጋሪ ወንዞች፣ የተበላሸ ምርጫ በአፍሪካ ቀንድ ቀጣና ሰላምና መረጋጋት እንዳይኖር ከፍተኛ ተጽእኖ ማሳደሩን ኢትዮጵያ አስረድታለች ብለዋል።
ከዚህም በተጨማሪ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን፤ ከጀርመን፣ ስዊድንና አየርላንድ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ጋር ውጤታማ የሁለትዮሽ ውይይት ማድረጋቸውን ገልጸዋል።
በሰሜን ኢትዮጵያ የተከሰተው የፀጥታ ችግር በህወሓት ተንኳሽነት መሆኑን ለአለም አቀፉ ማህበረሰብ አሳውቃለችም ነው ያሉት።
ኢትዮጵያ ችግሩን በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት ለምታደርገው ጥረት ድጋፍ ማድረግ አስፈላጊ መሆኑን መግለጻቸውንም ጠቁመዋል፡፡
ስድስተኛው የአፍሪካ ህብረትና የአውሮፓ ህብረት የጋራ ጉባኤ፣ ስምንተኛው የሙኒክ የሰኪዩሪቲ ኮንፈረንስና የሁለትዮሽ ውይይቶች በጥቅሉ ውጤታማ እንደነበሩ አምባሳደር ዲና በሳምንታዊ መግለጫቸው አብራርተዋል።