ለሀገር ዘላቂ ሰላምና ልማት መጠናከር መንግስት ትኩረት መስጠቱን አሳይቷል- የጋምቤላ ከተማ ነዋሪዎች - ኢዜአ አማርኛ
ለሀገር ዘላቂ ሰላምና ልማት መጠናከር መንግስት ትኩረት መስጠቱን አሳይቷል- የጋምቤላ ከተማ ነዋሪዎች
ጋምቤላ፣ የካቲት 16/2014(ኢዜአ) ለሀገር ዘላቂ ሰላም፣ አንድነትና ልማት መጠናከር መንግስት ትኩረት መስጠቱን ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በሰጠት ማብራሪያ በግልጽ እንዳሳዩ የጋምቤላ ከተማ ነዋሪዎች ገለጹ።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከምክር ቤቱ ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች የሰጡት ምላሽና ማብራሪያ አግባብነት ያላቸውና አጥጋቢ እንደነበሩ ነው ነዋሪዎቹ ለኢዜአ በሰጡት አስተያየት የተናገሩት።
በዚህም በዋናነት ሀገራዊ ሰላም፣ አንድነትንና የህዝብን የልማት ተጠቃሚነት ማረጋገጥ ላይ ትኩረት መደረጉን በግልጽ አሳይተዋል።
ማብራሪያውን በመገናኛ ብዙሃን መከታተላቸውን በመግለጽ አስተያየታቸውን ከሰጡ ነዋሪዎቹ መካከል አቶ መላኩ ኢታና፤ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በኢኮኖሚያዊ፣ ዲፕሎማሲያዊና ሌሎች ጉዳዮች ላይ የሰጡት ማብራሪያ ተገቢነት እንዳላቸው ነው ያመለከቱት።
በተለይም ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብን በማስመልከት በሰጡት ማብራሪያ አድናቆት እንዳላቸው ገልጸዋል።
ሆኖም ጠቅላይ ሚኒስትሩ በኦሮሚያ እና አፋር ክልሎች ከሰላምና ጸጥታ ጋር በተያያዘ በሰጡት ማብራሪያ በተወሰነ ደረጃ ቅሬታ እንዳለቸው ጠቁመው፣ "መንግስት የህዝቦችን ሰላም የማስጠበቅ ኃላፊነቱን በተሻለ ሊወጣ ይገባል" ብለዋል።
እየተስተዋለ ያለውን የኑሮ ውድነትና የመፍትሄ አቅጣጫን አስመልክተው በጠቅላይ ሚኒስትሩ የተሰጠው ምላሽ ግልጽና ይህንንም በተገቢው መረዳታቸውን የገለጹት ደግሞ ሌላው የጋምቤላ ከተማ ነዋሪ አቶ ማሉት ቶክ ናቸው።
ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ምላሽና ማብራሪያ መንግስት የተስተዋለውን የኑሮ ውድነት ለማርገብ እየሰራ ስለመሆኑ መገንዘባቸውንና በዚህም መሻሻል ይኖራል ብለው ተስፋ እንደሚያደርጉ ተናግረዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከደቡብ ሱዳን የሚመጣው የሙርሌ ጉሳ በጋምቤላ ክልል እያደረሰ ያለውን ችግር በዲፕሎማሲ ለመፍታት እየተደረገ ያለውን ጥረት አስመልክተው የሰጡት ማብራሪያ መንግስት ለችግሩ ትኩረት መሰጠቱን እንደሚያሳይም ገልጸዋል።
ሌላው የከተማው ነዋሪ አቶ ገቢ ገለቶ፤ ጠቅላይ ሚኒስትሩ የተወሰኑ እስረኞች መለቀቅን ቂም በቀልን ለማስወገድና የሀገርን ሰላም ለማስጠበቅ ሲባል ነው ማለታቸው ለቀጣይ ሀገራዊ ሰላም ዘላቂነት ፋይዳው የጎላ በመሆኑ እንደሚደግፉት ተናግረዋል።
በቀጣይ የሚጠበቀው ሀገራዊ ምክክር የኢትዮጵያን ህዝቦች አንድነት፣ ዘላቂ ሰላምና ልማትን ለማጠናከር እንደሚበጅ ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ማብራሪያ መረዳታቸውን ገልጸዋል።
አስተያየት ሰጪው እንዳሉት፤ መንግስት በማያግባቡ ጉዳዮች ላይ ተወያይቶ ችግሮችን ለመፍታት ከማንም በላይ ህዝብ ወሳኝ መሆኑን የገለጹበት ንግግርም ለህዝብ ውሳኔና የእርስ በርስ መከባበር ያላቸውን እምነት ያሳየ ነው።