አገራዊ ምክክሩ ለዘመናት ሲንከባለሉ የመጡ ችግሮችን ለመፍታት የሚያስችል ነው - ኢዜአ አማርኛ
አገራዊ ምክክሩ ለዘመናት ሲንከባለሉ የመጡ ችግሮችን ለመፍታት የሚያስችል ነው
የካቲት 16/2014/ኢዜአ/ አገራዊ ምክክሩ ለዘመናት ሲንከባለሉ የመጡ ችግሮችን ለመፍታት የሚያስችል መሆኑን ኢዜአ ያነጋገራቸው በአዲስ አበባ የሚኖሩ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ገለጹ፡፡
በኢትዮጵያ ያሉ ቁርሾዎችን ለማከም እና የተሻለ ነገን ለመገንባት የሚያስችል አገራዊ ምክክር ለማድረግ ኮሚሽን የተቋቋመ ሲሆን፤ በቅርቡም የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የኮሚሽነሮችን ሹመት ማጽደቁ ይታወቃል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ ትናንት ከህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች በሰጡት ማብራሪያም አገራዊ ምክክሩ አካታችና አሳታፊ ሊሆን እንደሚገባ መናገራቸው ይታወሳል፡፡
በተለይ የፖለቲካ ፓርቲዎች እድሉን በአግባቡ እንዲጠቀሙ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጥሪ አድርገዋል፡፡
ኢዜአ ያነጋገራቸው በመዲናዋ የሚኖሩ የተለያዩ የኀብረተሰብ ክፍሎች አገራዊ ምክክሩ ለረዥም ዘመናት ሲንከባለሉ የመጡ ችግሮችን በመፍታት በኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላምን ለማስፈን ሚናው የጎላ መሆኑን ይገልጻሉ፡፡
አርቲስት አመልማል አባተ አለመግባባቶችን በኃይል ለመፍታት መሞከር ለማንም የማይጠቅም አክሳሪ አካሄድ ነው ትላለች፡፡
በመሆኑም ችግሮችን በንግግር የመፍታት ባህል ከታች ከቤተሰብ ጀምሮ ሊጎለብት እንደሚገባም ነው የተናገረችው፡፡
ሁሉም የኀብረተሰብ ክፍል ችግሮችን በምክክር እንዲፈታ በቀና ልብ መስራት እንዳለበትም ነው ጥሪ ያቀረበችው፡፡
ሌላኛው የመዲናዋ ነዋሪ ኢንጂነር አበበ ጋሻው በበኩላቸው በተለይ የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች ለአገራዊ ምክክሩ በቅንነት ሊሰሩ እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡
ተቀራርቦ በመነጋጋር በርካታ ችግሮችን በቀላሉ መፍታት እንደሚቻል በመጠቆም፡፡
በአገር አቀፍ ደረጃ ያሉ ችግሮችን በውይይት ለመፍታት የተጀመረው ጥረት የሚበረታታ መሆኑን የተናገረችው ደግሞ ጋዜጠኛ የምስራች አጥናፍ ናት፡፡
ይህም በኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላምን ከማስፈን ባሻገር ችግሮችን በውይይት የመፍታት ባህልን እንደሚያጎለብት ጠቁማ፤ ለአገራዊ ምክክሩ መሳካት እያንዳንዱ ዜጋ ኃላፊነት እንዳለበት ተናግራለች፡፡
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በዋና ዋና አገራዊ ጉዳዮች ላይ ብሔራዊ መግባባት ለመፍጠር ያስችላል የተባለውን የኢትዮጵያ አገራዊ ምክክር ኮሚሽን ማቋቋሚያ አዋጅ ቁጥር 1265 /2014 ማጽደቁ ይታወሳል።
ምክር ቤቱ ከጥቂት ቀናት በፊት ባካሄደው ስብሰባ አገራዊ የምክክር ኮሚሽኑን የሚመሩ የ11 ኮሚሽነሮችን ሹመት በአብላጫ ድምጽ ማጽደቁም የሚታወስ ነው፡፡