በኢትዮጵያ የዴሞክራሲ ተቋማት የአሰራር ግልጽነትና ገለልተኝነት በተግባር እየተረጋገጠ መጥቷል - ኢዜአ አማርኛ
በኢትዮጵያ የዴሞክራሲ ተቋማት የአሰራር ግልጽነትና ገለልተኝነት በተግባር እየተረጋገጠ መጥቷል
የካቲት 16 ቀን 2014 (ኢዜአ) በኢትዮጵያ የዴሞክራሲ ተቋማት የአሰራር ግልጽነትና ገለልተኝነት በተግባር እየተረጋገጠ መምጣቱን በጠቅላይ ሚኒስትር ፅህፈት ቤት የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ማዕከል አስተባባሪ ሚኒስትር ዶክተር ቢቂላ ሁሪሳ ገለጹ።
ኢትዮጵያ በሕዝቦች ዘንድ ተቀባይነት ያለው ዴሞክራሲያዊ የአስተዳደር ስርዓት ለመገንባት የተለያዩ ጥረቶችን እያደረገች ትገኛለች።
ለዚህም ጠንካራ የዴሞክራሲ ስርዓት መገንቢያ ተቋማት ገለልተኝነትና ግልጽነት ባለው መልኩ ስራቸውን እንዲያከነወኑ ለማድረግ እየተሰራ ነው።
በጠቅላይ ሚኒስትር ዕህፈት ቤት የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ማዕከል አስተባባሪ ሚኒስትር ዶክተር ቢቂላ ሁሪሳ፤ ከኢዜአ ጋር በነበራቸው ቆይታ እንዳሉት መንግስት በዜጎች አመኔታ ያለው ተጨባጭ የዴሞክራሲ ስርዓት የመገንባት ስራ እያከናወነ ይገኛል።
ከለውጡ ማግስት ጀምሮ እስካሁን ነጻና ገለልተኛ የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን መፍጠር፣ ጠንካራ ምርጫ ቦርድ ማደራጀትና የፍትህ ስርዓቱን የማሻሻል ስራዎች መከናወናቸውን ጠቅሰዋል።
በተለይም በሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን በኩል ነፃና ገለልተኛ ተቋም የመፍጠር ተግባር እውን በመሆኑ "ለማመን የሚከብዱ" ሪፖርቶች እየወጡ ይገኛሉ ብለዋል።
የኮሚሽኑ ሪፖርት ላይ መንግስት የራሱ እይታ ቢኖረውም ለዜጎች መብት መከበር ግን ተስፋ ሰጭ ክንውኖች መታየታቸውን ገልጸው ተጠናክሮ እንዲቀጥል አስፈላጊው ድጋፍ ይደረጋል ሲሉ ዶክተር ቢቂላ ገልጸዋል።
ሌላው የዴሞክራሲ ስርዓት ከሚጠናከርበት መንገድ አንዱ ነጻ፣ ገለልተኛና ፍትሓዊ የምርጫ ስርዓት መሆኑን ይጠቅሳሉ።
በመሆኑም የኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ ከሌሎች አካላት የፖለቲካ ፍላጎትና ጣልቃ ገብነት ነፃ ሆኖ የአገሪቷን የምርጫ ሂደት እየመራ ይገኛል ብለዋል።
በእነዚህና ሌሎችም ተጨምረውበት በኢትዮጵያ የዴሞክራሲ ተቋማት የአሰራር ግልጽነትና ገለልተኝነት በተግባር እየተረጋገጠ መምጣቱን ዶክተር ቢቂላ ገልጸዋል።
የፍትህ ተቋማትም ነጻና ገለልተኛ ሆነው ዜጎችን እንዲያገለግሉ የተለያዩ ስራዎች መሰራታቸውን ሚኒስትሩ አንስተዋል።
አሁን በተጀመረው መልኩ የፍትህ ዘርፍ ማሻሻያው ቀጥሎ በኢትዮጵያ ዘላቂና እውነተኛ የዴሞክራሲ ስርዓት እውን ይሆናል ብለዋል።
በኢትዮጵያ ጠንካራና እውነተኛና የዴሞክራሲያዊ ስርዓት ሳይገነባ በመቆየቱ አገሪቷ በችግር አዙሪት ውስጥ እንድትቆይ ማድረጉ ይታወቃል።