ሁሉም ዜጋ ለሀገር ልማት የድርሻውን መወጣት እንዳለበት ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ማብራሪያ ተገንዝበናል- የሐረር ነዋሪዎች - ኢዜአ አማርኛ
ሁሉም ዜጋ ለሀገር ልማት የድርሻውን መወጣት እንዳለበት ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ማብራሪያ ተገንዝበናል- የሐረር ነዋሪዎች
ሐረር ፤ የካቲት 16 ቀን 2014(ኢዜአ) የሀገር ደህንነትና ልማትን አጠናክሮ ለማስቀጠል ሁሉም ዜጋ የድርሻውን መወጣት እንዳለበት ከጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ ማብራሪያ መገንዝባቸውን የሐረር ከተማ ነዋሪዎች ገለጹ።
ነዋሪዎቹ ለኢዜአ እንዳሉት፤ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ለተነሱት ጥያቄዎች የሰጡትን ማብራሪያ ከመገናኛ ብዙሃን ተከታትለዋል።
በተለይ ሀገራዊ ምክክር አለመግባባቶችን አቻችሎ መፍትሄ እንደሚያመጣ ከማብራሪያው ግልጽ እንደሆነላቸው ተናግረዋል።
የከተማው ነዋሪ አቶ መንግስቱ ከቼ ገለታ ሀገሪቱን እየፈተነ የሚገኘውን ሙስና ለመከላከል ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሰጡት ቁርጠኝነት የታከለበት ማብራሪያ ለሀገር እድገት ጠቀሜታው የጎላ እንደሆነ ነው ያመለከቱት።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሀገርን ጸጥታና ደህንነት ለማረጋገጥ የተከናወነውን ስራና ህዝቡ ማድረግ የሚጠበቅበትን ሃላፊነት ከመወጣት አንጻር የጠቆሙት ሃሳብ ትክክለኛ እና አግባብነት እንዳለው መገንዘባቸውን ተናግረዋል።
ሌላው የሐረር ከተማ ነዋሪ መምህር ቶማስ ቦጋለ ሁሉም ዜጋ ለሀገር ደህንነትና ልማት የበኩሉን መወጣት እንዳለበት ከማብራሪያው መገንዘባቸውን ነው የተናገሩት።
የጠቅላይ ሚኒስትሩ ገለጻና ማብራሪያ ኢትዮጵያ በውጭ እና በሀገር ውስጥ ያሉትን ጫናዎች በመቋቋም ያከናወናቻቸው ውጤታማ የልማት ስራዎች ግልጽ ያደረገ ነው ብለዋል።
በተለይ ሀገራዊ ምክክሩ አለመግባባቶችን አቻችሎ መፍትሄ እንደሚያመጣ ከማብራሪያው መረዳታቸውን ገልጸዋል።
በዚህም ዘላቂ ሰላምና ብሔራዊ መግባባት እንደሚመጣ ተስፋ እንደሚያደርጉ የተናገሩት መምህር ቶማስ፤ ይህም አንድነትን በማጠናከረ የውጭ ጫናን በዘላቂነት ለመቋቋም እንደሚያመች አብራርተዋል።
አቶ ውብሸት ወርቁ በበኩላቸው በተለይ ከንግድ እንቅስቃሴ ጋር በተያያዘ የገቢ እና ወጪ ንግድ አለመጣጣም ያሳደረውን ተጽዕኖ ጠቅላይ ሚኒስትሩ የገለጹበት ሁኔታ አጥጋቢ መሆኑን ጠቅሰው፤ በተለይ ጦርነት ባለበት ሀገር ኢኮኖሚው እንዳይጎዳ የተከናወነው ስራ ጥሩ እንደሆነ መገንዘባቸውን ገልጸዋል።
ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ሃይል ማመንጨቱ ከምንም በላይ አስደስቶኛልም ብለዋል።