ቀጥታ፡

የሰዎች ለሰዎች ድርጅት በጦርነቱ የተፈናቀሉ ወገኖችን የድጋፍና መልሶ ማቋቋም ስራ እያከናወነ ነው

የካቲት 16 ቀን 2014 (ኢዜአ) አሸባሪው ህወሃት በከፈተው ጦርነት የተፈናቀሉና የንብረት ውድመት የደረሰባቸውን ወገኖች የድጋፍና መልሶ ማቋቋም ስራ እያከናወነ መሆኑን የሰዎች ለሰዎች ግብረ ሰናይ ድርጅት ገለጸ።

ድርጅቱ 40ኛ ዓመት የምሥረታ በዓሉን አስመልክቶ በቆይታው ባከናወናቸው ተግባራትና ቀጣይ ሥራዎቹ ዙሪያ መግለጫ ሰጥቷል።

በድርጅቱ የኢትዮጵያ ዳይሬክተር ተወካይ ታዬ ይልማ፤ በጦርነቱ ሳቢያ የተፈናቀሉና የንብረት ውድመት የደረሰባቸውን ወገኖች የመልሶ ማቋቋም ስራ እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

የድጋፍ ሥራውን ለማከናወን ድርጅቱ ለመነሻ 2 ሚሊዮን ዩሮ መድቦ ወደ ስራ መግባቱንም ጠቁመዋል።  

በአፋር እና አማራ ክልሎች በመጠለያ ለሚገኙ 50 ሺህ ወገኖች ድጋፍ ማድረጉን አንስተዋል።

የአየር ንብረት ለውጥ ለመቋቋም በሚደረገው የችግኝ ተከላ መርሃ ግብርም ድርጅቱ የደርሻውን ይወጣል ብለዋል።         

በዘንድሮው ዓመት ከ19 ነጥብ 4 ሚሊዮን በላይ ችግኞች እንዲተከሉ ዝግጅት መደረጉንም ተናግረዋል።   

በተለያዩ የአገሪቷ ክፍሎች ድርጅቱ ከ461 በላይ ትምህርት ቤቶችን በመገንባት ከ500 ሺህ በላይ ተማሪዎችን ተጠቃሚ ማድረጉንም አቶ ታዬ ገልጸዋል።    

የሙያ ሥልጠና የሚሰጥባቸው ስድስት ቴክኒካልና ቮኬሽናል ኮሌጆችም እንዲሁ አገልግሎት እየሰጡ መሆኑን ጠቁመዋል።      

በተያዘው ዓመት 9 አዳዲስ ትምህርት ቤቶችን ለመገንባት በጀት የተያዘ ሲሆን ከዚህ ቀደም ግንባታቸው የተጀመሩ 18 ትምህርት ቤቶችም ግንባታ የሚቀጥል ይሆናል።     

ድርጅቱ እስካሁን 7 ቢሊዮን ብር ወጪ በማድረግ የተለያዩ የልማት ተግባራት ያከናወነ ሲሆን በዚህም 6 ሚሊዮን ዜጎች ተጠቃሚ ሆነዋል ተብሏል።  

የሰዎች ለሰዎች ግብረ ሰናይ ድርጅት ባለፉት 40 ዓመታት በኢትዮጵያ የተለያዩ የልማት ስራዎችን አከናውኗል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም