ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የኢትዮጵያውያን በአንድነት የማሸነፍ ታሪክ ነፀብራቅ ነው-ምሁራን - ኢዜአ አማርኛ
ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የኢትዮጵያውያን በአንድነት የማሸነፍ ታሪክ ነፀብራቅ ነው-ምሁራን
ሚዛን፣ የካቲት 16/2014 (ኢዜአ) ኃይል ማመንጨት የጀመረው ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የኢትዮጵያውያን በአንድነት የማሸነፍ ታሪክ ነፀብራቅ ነው ሲሉ የሚዛን ቴፒ ዩኒቨርስቲ የታሪክ ምሁራን ተናገሩ።
ከኢዜአ ጋር ቆይታ ያደረጉት ምሁራን "ግድቡ ኢትዮጵያውያን በአንድነት ተነስተን ታሪክ መሥራት እንደምንችል በተግባር ያሳየንበትና በቀጣይም ታሪክ መሥራት እንደምንችል ያረጋገጥንበት ነው" ብለዋል።
የዩኒቨርሲቲው የታሪክ መምህር ዓለማየሁ አብርሃም "ኢትዮጵያዊያን ከአንድ ምዕተ ዓመት በፊት በአድዋ ወራሪውን የኢጣሊያ ጦር ድባቅ በመምታት የተጎናጸፍነውን ድል ዛሬም በትውልድ ቅብብሎሽ በህዳሴው ግድብ መድገማችንን ለዓለም አሳይተናል" ብለዋል።
ከግድቡ ኤሌክትሪክ በማመንጨት የኢትዮጵያውያን በአንድነት የማሸነፍ ታሪክ ነጸብራቅ፤ የ"እችላለሁ" ጠንካራ ወኔ በጦር ሜዳ ብቻ ሳይሆን፤ በልማትም መረጋገጡን ተናግረዋል።
በግድቡ የጀግና ልጅ የአባቱን ጀግንነት ከመናገር በዘለለ ጀግንነትን በራሱ ዘመን በተግባር ማሳየቱን መምህር ዓለማየሁ ገልጸዋል።
የትናንቱ የጦር ሜዳ ጀግንነት ዛሬ በልማት መደገሙን ''ታሪክ ራሱን ደግሟል'' በማለት ገልጸውታል መምህር ዓለማየሁ።
ትውልዱ ታሪክ ከመናገር ባለፈ ልዩነቶችን ወደ ጎን በመተው አባይን በመገደብ ኤሌክትሪክ እንዲያመነጭ ማድረጉ የአባቶቹን የድል አድራጊነት ፈለግ ተከታይ ትውልድ መፈጠሩን እንደሚያመላክት ገልጸዋል።
"ኢትዮጵያውያን ለዘመናት የኖረውን ''አባይ ግንድ ይዞ ይዞራል'' የሚለውን አባባል ኃይል በማመንጨት በመተካት በትውልዶች የሚነገር አዲስ ታሪክ በደማቅ ቀለም ጽፈናል" ብለዋል።
''የግድቡን ግንባታ ለማደናቀፍ እየተደረገ ያለውን ጫናና ትንኮሳ በአይበገሬነት በማለፍ ለዚህ ደረጃ መብቃት ትልቅ ኩራት ነው'' ያሉት ምሁሩ፣ግድቡን ኃይል ለማመንጨት ያበቁ የኢትዮጵያ ልጆች በተባበረ ክንድ ቀሪ ሥራዎችን ለማጠናቀቅ ትልቅ ሞራልና ጉልበት እንዳገኙ ነው የተናገሩት።
''አባይን ለመገደብ በቀዳማዊ ኃይሌ ሥላሴ የተጀመረው ራዕይ በእኛ ጊዜ ሆኖ ማየት መቻል አስገራሚ ነው'' ያሉት ደግሞ ሌላው የዩኒቨርሲቲው የታሪክ መምህር ደባሱ ተሾመ ናቸው።
"ኢትዮጵያ ምንም እንኳን ተግዳሮቶች ቢበዙባትም፤በትውልዶች ቅብብሎሽ በርካታ አስደማሚ ተግባራት እንደምትፈጽም ህዳሴው ግድብ አመላካች ነው" ብለዋል።
''ኃይል ለማመንጨት የበቃው ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የኢትዮጵያውያን የአንድነት መገለጫ ነው'' ሲሉም ተናግረዋል።
በአንድነት ተባባብሮ በመስራት ትልቅ ደረጃ ላይ መድረስ እንደሚቻል የህዳሴው ግድብ ህያው ምስክር እንደሆነም መምህር ደባሱ ገልጸዋል።
"አባይን ገድቦ ኃይል ለማመንጨት ዕድል የገጠመው ይህ ትውልድ፤ የግድቡን ቀሪ ግንባታ እንደሚያጠናቅቅና ሌሎች ሀገራዊ ፕሮጀክቶችን ገንብቶ ለማጠናቀቅ አቅም እንዳለው ለዓለም አሳይቷል" ብለዋል።
"ኢትዮጵያዊያን የ''እችላለሁ'' መንፈስና ትብብር በግድቡ ግንባታ እንዳሳየን ሁሉ፤ ሌሎች የመሠረተ ልማት አውታሮችን በመገንባት የዕድገት ጉዟችንን ለማፋጠን መትጋት አለብን" ብለዋል።
ኢትዮጵያ ላለፉት 11 ዓመታት ግንባታውን እያካሄደች ካለችው የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ባለፈው እሁድ ከአንድ ተርባይን 375 ሜጋ ዋት ማመንጨት እንደጀመረች መዘገቡ ይታወሳል።
ግድቡ ከ13 ተርባይኖች ከ5ሺህ በላይ ሜጋ ዋት ሀይል እንዲያመነጭ በመገንባት ላይ እንደሚገኝ መረጃዎች ያመለክታሉ።