ኢትዮጵያ ከታላቁ የህዳሴ ግድብ ኃይል ለማመንጨት ከማንም ፈቃድ ለመጠየቅ የገባችው የውል ስምምነት የለም

የካቲት 16 ቀን 2014 (ኢዜአ) "ኢትዮጵያ ከታላቁ የህዳሴ ግድብ ኃይል ለማመንጨት ከማንም ፈቃድ ለመጠየቅ የገባችው የውል ስምምነት የለም" ሲሉ የውሃ አስተዳደር አማካሪው አቶ ፈቅአህመድ ነጋሽ ገለጹ፡፡

ኢትዮጵያውያን እንደ ዓይናቸው ብሌን የሚጠብቁት ታላቁ የህዳሴ ግድብ ከ11 ዓመታት በኋላ የመጀመሪያውን ምእራፍ ኃይል የማመንጨት ስራ ጀምሯል፡፡

ከዓባይ ተፋሰስ 86 በመቶ ድርሻ ያላት ኢትዮጵያ "ዓባይ ግንድ ይዞ ይዞራል" ከሚል የቁጭት ዜማ ባለፈ ከወንዙ ጠብ የሚል ነገር ሳትጠቀም ዘመናትን ኖራለች፡፡

ቀናት በወራት ተተክተው ዓመታት እንደጅረት ተጉዘው ዓባይ ከባይተዋርነት ወጥቶ ለዚህ ዘመን ትውልድ ብርሃን ሊሰጥ ስራውን አሃዱ ብሎ ጀምሯል፡፡

አጠቃላይ የግንባታ ሂደቱ 84 በመቶ የደረሰው ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ካሉት 13 ተርባይኖች "ዩኒት 10" የተሰኘው ተርባይን 375 ሜጋ ዋት ኃይል ማመንጨት ጀምሯል፡፡

ነገር ግን ግብጽና ሱዳን ግድቡ ሀይል ማመንጨት መጀመሩ በተበሰረ በሰዓታት ልዩነት "ኢትዮጵያ ሶስቱ አገራት በካርቱም የፈረሙትን የመርሆች ስምምነት በመጣስ ኃይል አመነጨች" ሲሉ የተለመደ ክሳቸውን አሰምተዋል፡፡

ጉዳዩን በሚመለከት ኢዜአ ያነጋገራቸው የውሃ አስተዳደር አማካሪው አቶ ፈቅአህመድ ነጋሽ ፤ ግብጽና ሱዳን "ተጥሷል" በሚሉት የመርሆች ስምምነት ኢትዮጵያ ኃይል እንዳታመነጭ የሚከለክል አንቀጽ የለም ይላሉ፡፡

የኢትዮጵያ፣ግብጽና ሱዳን መሪዎች እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር በ2015 በሱዳን ርዕሰ መዲና ካርቱም የተፈራረሙትን የመርሆች ስምምነት ግብጽና ሱዳን ሆነ ብለው በተሳሳተ መንገድ እየተረጎሙት መሆኑንም ነው የተናገሩት፡፡

የመርሆች ስምምነት አንቀጽ 5 ሶስቱ አገራት "በመመሪያው ላይ ይስማማሉ፤የግድቡ ግንባታ በትይዩ ይካሄዳል" እንደሚል ጠቅሰው፤ ከዚህ ውጪ "ውሃ ለመሙላት ይስማማሉ" የሚል ሃሳብ እንደሌለው አብራርተዋል፡፡

"የግድቡ ግንባታ በትይዩ ይካሄዳል" ማለት ደግሞ ግድቡ ኃይል ማመንጫ በመሆኑ የውሃ አሞላል፣አለቃቀቅና ኃይል ማመንጨትን ይጨምራል ብለዋል፡፡

ከዚህ አኳያ ግብጽና ሱዳን የግድቡን ኃይል ማመንጨት የሚቃወሙት እንደ አውሮፓውያን የዘመን ቀመር በ1929 እና 1959 ውሃውን በብቸኝነት ለመቆጣጠር ያወጡት ህግ እንዳይነካባቸው በማሰብ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ነገር ግን ኢትዮጵያ ሶስቱ አገራት በመርሆች ስምምነት መመሪያ ከተስማሙ በመመሪያው መሰረት፤ካልተስማሙ ደግሞ በራሷ መንገድ ግድቡን መሙላት፣ውሃ መልቀቅና ኃይል ማመንጨት እንደምትችል ጠቁመዋል፡፡

ግብጽ "እኔ ብቻ ልልማ ሌሎች የዳር ተመልካች ይሁኑ" የሚል አካሄድ እንጂ የግድቡ ኃይል ማመንጨት ጉልህ ጉዳት እንደማያደርስባት ጠንቅቃ ታውቃለች ብለዋል፡፡

የአስዋን ግድብ ለሁለት ዓመታት የሚያገለግል ውሃ የመያዝ አቅም እንዳለው የገለጹት አቶ ፈቅአህመድ፤ የህዳሴው ግድብ የሚይዘው ውሃ እስከሚለቀቅ የሚቀንሰው በትነት ከሚጠፋው ብዙም አይበልጥም ብለዋል፡፡

ግብጽ በአጠቃላይ ካላት የውሃ አቅም ጋር ሲነጻጸር ግድቡ የሚቀንሰው ከአንድ በመቶ በታች ነው፤ይሄ ደግሞ በማንኛውም መመዘኛ ጉልህ ጉዳት የሚያደርስ አይደለም ነው ያሉት፡፡

ግብጽ በህገ መንግስቷ አንቀጽ 44 ላይ ያሰፈረችው "መንግስት በናይል ወንዝ ላይ ያላትን ታሪካዊ መብት ይከላከላል" የሚለው አገላለጽ ለሌሎች የተፋሰሱ አገራት እውቅና ያልሰጠና የራስ ወዳድነትን ሃሳብ የሚያሳይ መሆኑንም አብራርተዋል፡፡

በህገ መንግስቱ የተገለጸው ሃሳብ የ1929 እና 1959 የቅኝ ገዥዎች ስምምነት ማስጠበቂያ መሆኑን ጠቅሰው፤ከዚህ አኳያ ግብጽ የምታሰማው ተቃውሞ ይህንኑ ጥቅም ከማስጠበቅ የመነጨ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ኢትዮጵያ በግብጽ ለተፈረሙ ሁሉም የውሃ ስምምነቶች እውቅና አልሰጠችም፤ባልፈረመችውና እውቅና ባልሰጠችው ህግ ተጠያቂ አትሆንም ብለዋል፡፡

ኢትዮጵያ የየትኛውንም አገር ጥቅም ሳትጎዳ የራሷን ፕሮጀክት በራሷ መንገድ መስራት ትችላለችም ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም