ሕዳሴ ግድብ ሃይል ማመንጨት መጀመሩ ኢትዮጵያን ወደ አዲስ ምዕራፍ ለማሸጋገር የጎላ አስተዋፅኦ አለው - ኢዜአ አማርኛ
ሕዳሴ ግድብ ሃይል ማመንጨት መጀመሩ ኢትዮጵያን ወደ አዲስ ምዕራፍ ለማሸጋገር የጎላ አስተዋፅኦ አለው
የካቲት 16 ቀን 2014 (ኢዜአ)ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ሃይል ማመንጨት መጀመሩ ኢትዮጵያን ወደ አዲስ ምዕራፍ ለማሸጋገር የጎላ አስተዋፅኦ የሚኖረው መሆኑን የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ተናገሩ።
በኢትዮጵያውያን የራስ አቅም እየተገነባ ያለውን ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የኤሌክትሪክ ሃይል ማመንጨት መጀመሩ በትብብር ውጤት ማምጣት እንደሚቻል አመላክቷል ብለዋል።
የምክር ቤት አባል ዶክተር ብርሃነመስቀል ጠና፤ የህዳሴ ግድብ የኤሌክትሪክ ሃይል ማመንጨት መጀመሩ የታሰበውን ውጤት ማሳካት የተቻለበት ትክክለኛ ማሳያ መሆኑን ገልጸዋል።
የህዳሴ ግድብ የትብብርና አንድነት ተምሳሌት መሆኑን ጠቅሰው የአመራር ጥበብ፣ የሊህቃን እውቀት፣ገንዘብና ሁሉም በአቅሙ አሻራውን ያሳረፈበት ብርሃን መታየት የጀመረበት ታሪካዊ አጋጣሚ ነው ብለዋል።
የፕሮጀክቱ እውን መሆን የማይቻለውን ማሳካት፣ድህነትን ማሸነፍ እንደሚችሉ ያሳየ በመሆኑ በቀጣይም ትብብርና አንድነትን በማጠናከር ውጤት ለማስመዝገብ መስራት ያስፈልጋል ነው ያሉት።
ሌላኛዋ የምክር ቤት አባል ወይዘሮ መስከረም ሃይሉ፤የፕሮጀክቱ ግንባታ ቀደም ሲል በነበረው ችግር በታቀደው ልክ መሄድ ባይችልም ባለፉት 4 አመታት በተሰጠው ወሳኝ የአመራርና ቁርጠኝነት ፍሬውን ማየት እንዳስቻለ ገልጸዋል።
ግድቡ ሃይል ማመንጨት መጀመሩ የኢትዮጵያን የብልጽግና ተስፋ ከፍ ያደረገና የህዝብን ተጠቃሚነት እውን ያደረገ መሆኑን ተናግረዋል።
የህዳሴ ግድብ ኢትዮጵያውያን ተግባቦት የፈጠሩበትና የተሳሰሩበት የአንድነት ፕሮጀክት መሆኑን የገለጹት ደግሞ ሌላኛው የምክር ቤት አባል አቶ አኔሳ መልኩ ናቸው።
ግድቡ የኤሌክትሪክ ሃይል ማመንጨት መጀመሩ ከኢትዮጵያም አልፎ ለሌሎች የአፍሪካ አገራት ትልቅ ተስፋ የሰነቀ መሆኑን ጠቁመዋል።
በምጣኔ ሃብት በእድገት ላይ ላሉ አገራት ጭምር ተምሳሌት እንደሚሆንም ገልጸዋል።
የተጀመሩና በቀጣይ የሚጀመሩ ግዙፍ የልማት ፕሮጀክቶችንም ለውጤት ማብቃት እንደሚቻል ማሳያ እንደሆነ አብራርተዋል።
ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የመሰረት ድንጋይ ከተቀመጠበት መጋቢት 24 ቀን 2003 ዓ.ም ጀምሮ ላለፉት 11 ዓመታት መላ ኢትዮጵያውያን በሞራል፣በገንዘብና በጉልበት ጭምር ድጋፍ አድርገዋል።
የግድቡ ግንባታ በስኬት እየተከናወነ ሲሆን ካሉት 13 ተርባይኖች አንደኛው ከቀናት በፊት 375 ሜጋ ዋት ሃይል ማመንጨት መጀመሩ ይታወሳል።