ከ11 ዓመታት በኋላ የተገኘች ተናፋቂዋ የሐሴት ቅጽበት ከጉባ ሰማይ ሥር - ኢዜአ አማርኛ
ከ11 ዓመታት በኋላ የተገኘች ተናፋቂዋ የሐሴት ቅጽበት ከጉባ ሰማይ ሥር
አዲስ አበባ የካቲት 14/2014 /ኢዜአ/ የዓለማችን ወንዞች ንጉስ ዓባይ ታሪክና ባህል ሊቀይር የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ሲወጠን ከውጥኑ እስካሁኑ አካለ መጠን መድረስ የእልፍ ሠራተኞች ትጋትና መስዋዕትነት አለበት።
ከሰሞኑ ዓባይ ወንዝ የብርሃን ወጋገን ሲፈነጥቅ በተስፋ የናፈቁ መላው ኢትዮጵያዊያን በሐሴት ቢፈነድቁም ውሎ አዳራቸውን በጉባ ሰማይ ሥር ካደረጉ የግድቡ ሠራተኞች ፌሽታ ጋር ግን የሚስተካከል አይሆንም።
ከግድብ ቁፋሮ እስከ ኃይል ማመንጨት ጅማሮ የዘለቀው የ11 ዓመታት ጉዞ ውጫዊና ውስጣዊ ጫናዎች ባለፈ በግንባታ ሂደቱ ካጋጠሙ ውጣ-ውረዶች ሳይበገሩ የላብና ድካም ውጤታቸውን በአካል ሲመለከቱ ሐሴታቸው ከቃላት በላይ ነበር።
በአፍሪካ ግዙፍነትን በተላበሰው ግድብ ግንባታ ላይ አሻራቸውን ያኖሩ ክንዶችና አዕምሮዎች ከ11 ዓመታት በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ የፈነጠቀውን የብርሃን ብስራት በደስታ ያጣጣሙበት ቅጽበት ሆኗል።
በኃይል ማመንጫ ግድብ ግንባታው የሚሳተፉ በ10 ሺዎች የሚቆጠሩ ሠራተኞች በሙያ፣ በአካባቢና ማንነት የተለያዩ ሆነው ግድቡ ግን ያስተሳሰራቸው ዜጎች ናቸው።
በተለያዩ ሙያ ዘርፎች ልምድ እያካበቱ፣ አገርን ለብርሃን ጸጋ ያላበሱ ባለሙያዎች የ11ኛ ዓመት የሥራ ጓደኝነት በዓላቸውን በኃይል ማመንጫው ዋዜማ ጉባ ላይ በድምቀት አክብረዋል።
ከ11 ዓመታት በኋላ የደስታ በዓላቸውን ሲያከብሩ ግን በእነዚህ የውጣ-ውረድ ዓመታት በግድቡ ላይ አሻራቸውን አሳርፈው በተለያዩ ምክንያቶች ህይወታቸውን ያጡ ሰራተኞችን በማሰብ ነበር።
ኢዜአም የሠራተኞቹን የደስታ ምሽት ታድሞ የድል ሰርገኞችን አነጋግሯል።
አቶ እስጢፋኖስ ሰለሞን እና አቶ ሰብስቤ አወል በግልገል ጊቤ እና ጣና በለስን ጨምሮ በተለያዩ የኃይል ማመንጫ ግድቦች ለአሥርት ዓመታት በምህንድስና ስራ አገልግለዋል።
የ11 ዓመታት የሕዳሴ ግድብ ቆይታቸው ግን ልዩ ገጽታ እንዳለው ገልጸው፤ ከግድቡ ጅማሮ እስካሁን ባሉት ዓመታት ከጨለማ ወደ ብርሃን የተሻገርንበት ነው ብለዋል።
በጉባ ከባድ የአየር ንብረትና በመልከ ብዙ ችግሮች ተሻግረን የዓባይን ወንዝ ወደ ብርሃን መለወጣችን ከህዝቡ ደስታ በላይ የሠራተኞች ሐሴት ወደር የለውም ይላሉ።
የበሽታዎች ወረርሽኝ ሥርጭት በሚበዛበት የግድቡ አካባቢ በጤናው ዘርፍ የፋርማሲ ክፍል ኃላፊ አሸናፊ ሞገስ ከሌሎች የአገሪቷ አካባቢዎች ቆይታቸው ይልቅ የህዳሴው ግድብ ልዩ እንደሆነ ነው የተናገሩት።
የሕዳሴ ግድብ ቆይታቸው እናት አርግዛ እስክትወልድ እንዳለው ስሜት በመሆኑ ‘ግድቡ ኃይል ሲያመነጭ በአካል መመልከቴ ደስታውም እጥፍ ድርብ ነው’ ይላሉ።
ለ11 ዓመታት በሥራ ላይ ያሳለፉ ሠራተኞች የየካቲት 13ን ያህል የደስታ ምሽት የማጣጣም ጊዜ እንዳልነበራቸው የሚናገረው ደግሞ የምህንድስና ባለሙያው ዘላለም አድማሱ ነው።
በግድቡ በሠራተኞች ተጋድሎ ‘ኢትዮጵያዊያን ጨለማውን በብርሃን መግፈፍ ጀምረዋል፤ እኛም የአባይ ዘመን ልጆች የመባል ደማቅ ታሪክ ተጎናጽፈናል’ ይላል።
የ11 ዓመታት ቆይታ ሌላው ትሩፋት የውጭ ዜጋን ጨምሮ የማይተዋወቁ ሠራተኞችን ማህበራዊ መስተጋብርን ያጠናከረ፤ የሙያ ልምድን ያለዋወጠ አጋጣሚ መሆኑ ነው።
የኢትዮጵያን አንጡራ ሀብት ባሰባሰበው በዚህ ግድብ ሠራተኞች ከጋብቻ ጀምሮ ማህበራዊ ግንኙነትና የመቻቻልን እሴት በማጠናከር ሥፍራውን ትንሿ ኢትዮጵያ እንዳሰኘው ይገልጻሉ።
ግድቡ ከኢትዮጵያ አልፎ ለአፍሪካና ለዓለም የሚሰጠው ጥቅም ከፍተኛ የሆነ ፕሮጀክት እንደሆነ የሚናገሩት ሙያተኞቹ፤ እስካሁን ውጣ-ውረዱን እንዳሳለፉ ሁሉ እስከ ፕሮጀክቱ ፍጻሜ በጽናትና በትጋት እንደሚቀጥሉ ይናገራሉ።
ፕሮጀክቱ ላለፉት ሦስት ዓመታት በግድቡ ግንባታ ላይ የተሰራው የለውጥ ሥራም ግንባታው እንዲፋጠን የተሻለ ውጤት እንዲመጣ እንዳስቻለ ገልጸዋል።
የሥራው ቅልጥፍናም ለሌሎች ፕሮጀክቶች ምሳሌ እንደሚሆን ገልጸው፤ መንግስት የሚያጋጥሙ ክፍተቶችን እንዲያሟላ ጠይቀዋል።
በፕሮጀክቱ የእስካሁኑ ስኬት በርካታ ሠራተኞች የህይወት መስዋዕትነት ጭምር መክፈላቸውን አስታውሰው ለሠራተኞች አንዳንድ ማበረታቻዎች እንዲሟሉም ጠይቀዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የግድቡን ግንባታ እያከናወኑ ያሉ ሠራተኞች "የአገርን ሕልውና ለመታደግ በተደረገው ጦርነት መሳተፍ እንፈልጋለን፤ ግን ግድቡ እንዲቆም አንፈልግም" ማለታቸውን ጠቅሰው አመስግነዋል።