ቀጥታ፡

በኢትዮጵያ ጥራት ያለው የቴሌኮም አገልግሎት ለመሥጠት እየሰራሁ ነው- ሳፋሪኮም

የካቲት 15 ቀን 2014 (ኢዜአ) ሳፋሪኮም በኢትዮጵያ ጥራት ያለው የቴሌኮም አገልግሎት ለመሥጠት እየሰራ መሆኑን አስታወቀ፡፡

"ዓለም አቀፍ ትብብር ለኢትዮጵያ" የተሰኘው ጥምረት የሚመራው ሳፋሪኮም ኢትዮጵያ በ850 ሚሊዮን ዶላር ጨረታ አሸንፎ በኢትዮጵያ በቴሌኮም ሴክተር መሰማራቱ ይታወሳል።

በዚህም ኩባንያው በኢትዮጵያ በዘርፉ ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪ የሆነ የቴሌኮም አገልግሎት ለመሥጠት የሚያስችለውን የቴክኖሎጂ ማሟያ ሥራ እያከናወነ መሆኑን ገልጿል።

በዛሬው ዕለትም በአዲስ አበባ ያስገነባውን የመረጃ ቋት ማዕከል ለጋዜጠኞች አስጎብኝቷል።

የኩባንያው የውጭ ጉዳይና ቁጥጥር አፊሰር ማቴ ሃሪሰን ሃርቬይ፤ ሳፋሪኮም የኢትዮጵያ ሕዝብ የሚፈልገውን የቴሌኮም ጥራት ለማሟላት ትኩረት አድርጎ እየሰራ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

ዓለም አቀፍ ደረጃን የተላበሰ የአገልግሎት ተደራሽ በማድረግ የሚጠበቅበትን ግዴታ ለማሟላት እየሰራ መሆኑንም እንዲሁ፡፡

ኩባንያው በአሁኑ ወቅት በአዲስ አበባ የመረጃ ቋት ማዕከል የገነባ ሲሆን፤ በሌሎች የክልል ከተሞችም ቀስ በቀስ የተደራሽነት አድማሱን እያሰፋ እንደሚሄድም ገልጸዋል፡፡

ኩባንያው ከዚህ በተጓዳኝ የቴሌኮም አገልግሎት ለመሥጠት የሚያስችሉ ማማዎች ግንባታና የሰው ሃይል ቅጥር እየተከናወነ መሆኑንም ነው የጠቆሙት፡፡

የኢትዮ-ቴሌኮም የመሰረተ ልማት አገልግሎት ለመጠቀም የሚያስችለውን ውይይት እያደረገ ስለመሆኑ ጠቅሰው፤ ኩባንያው ከጥቂት ወራት በኋላ የድምጽ፣ የጽሁፍና የኢንተርኔት አገልግሎት ይጀምራል ነው ያሉት፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም