ቀጥታ፡

የሃይማኖት መሪዎች ለሀገራዊ ምክክሩ ስኬታማነት የድርሻቸውን እንዲወጡ ተጠየቀ

አዳማ ፤ የካቲት 15/2014(ኢዜአ) ሁሉን አካታች የሆነ ሠላምና ሀገረ መንግስት ግንባታ ላይ ለሚያተኩረው ሀገራዊ ምክክሩ ስኬታማነት የሃይማኖት መሪዎች የድርሻቸውን እንዲወጡ ተጠየቀ።
" በወቅታዊ የሃይማኖቶች ሁኔታ፣ተግዳሮቶችና እድሎች  ለአውንታዊ የሰላም ግንባታ " በሚል መሪ  ሃሳብ የሰላም ሚኒስቴርና የኢትዮጵያ ሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ በጋራ ያዘጋጁት የውይይት መድረክ  በአዳማ ከተማ እየተካሄደ ነው።

በመድረኩ ላይ የሰላም ሚኒስቴር የሰላም ግንባታና ብሔራዊ መግባባት ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ታዬ ደንደአ እንዳሉት፤ መንግስት በሃይማኖቶች ሃይማኖቶች በመንግስት ጉዳይ ጣልቃ የማይገቡ መሆኑን በህገ መንግስቱ በግልፅ ተደንግጓል።

ሆኖም  ሁላችንም መኖር የምንችለው አስተማማኝ ሰላም የሰፈነባትና የተረጋጋች ሀገር ስትኖረን ነው ብለዋል።

በዚህም የሃይማኖቶች መሪዎችንና ተከታዮቻቸው በሀገራዊ ምክክሩ ንቁ ተሳትፎ በማድረግ ስኬታማ እንዲሆን የበኩላቸውን እንዲወጡ ጠይቀዋል።

ዜጎች በሰላም ወጥተው እንዲገቡ፣ልማትና እድገት እንዲቀጥል ብሎም የተረጋጋች ሀገር ሊኖረን ይገባል ብለዋል ሚኒስትር ዴኤታው።

ኢትዮጵያ ሃይማኖቶችም፣ብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦችም በጋራ የተሳፈሩዋት ብቸኛ መርከብ ነች ያሉት አቶ ታዬ፤ ይችን መርከብ ማዕበል እንዳያናውጣትና እንዳትሰምጥ መጠበቅ ከሃይማኖት መሪዎችና ቤተ እምነቶቻቸው የሚጠበቅ ቀዳሚ ተግባር መሆኑን አመልክተዋል።

ይህ ካልሆነ ክርስቲያን፣ሙስሊም ፣ ዋቄፈታ ስለሆንን አንተርፍም፤ አብረን እንሰምጣለን ሃይማኖትን እንደመሳሪያ ተጠቅመው የራሳቸውን የከሰረ የፖለቲካ አጀንዳ በእምነት በማላከክ እናሳከለን ብሎ ማሰብ ቅዠት ነው ብለዋል።

የውይይት መድረኩ ሀገሪቱ  አሁን ካለችበት  ችግር ለማላቀቅ የሃይማኖት መሪዎችና ቤተ እምነቶቹ በቀጣይ ሀገራዊ ምክክሩ ውስጥ መጫወት የሚችሉትን ሚናና በሚያበርከቱት አስተዋጽኦ ላይ የተኮረ መሆኑን የገለጹት ደግሞ የኢትዮጵያ ሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ዋና ፀሓፊ ልቀ ትጉኋን ተጋይ ታደለ ናቸው።

የሀገር ሰላም እንዳይደፈርስ፣ ዜጎች እንዳይጎዱና ንብረት እንዳይጠፋ የሃይማኖት መሪዎች ቤተ እምነቶቻቸውንና ተከታዮቻቸውን በአግባቡ በመምራት የድርሻቸውን መወጣት እንደሚኖርባቸው አመልክተዋል።

ሀገራዊ የምክክር መድረኩ ሁሉን አካታች የሆነ ሠላምና ሀገረ መንግስት ግንባታ ላይ እንደሚያተኩር፤  ለዚህም ነጻና ገለልተኛ ተቋም ለመመስረት የሚያስችል ረቂቅ አዋጅና የሀገራዊ ምክክሩ ኮሚሽነሮች ሹመት  በኢፌዴሪ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ማጽደቁ ይታወቃል።

በመድረኩ ላይ ከሁሉም ሃይማኖቶች የተወከሉት የሃይማኖት መሪዎችና ተከታዮች እየተሳተፉ ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም