በአርሲ ዞን በ37 ሺህ ሄክታር መሬት ላይ በበጋ መስኖ ስንዴ እየለማ ነው

አዲስ አበባ የካቲት 14/2014 /ኢዜአ/የአርሲ ዞን ምክትል ዋና አስተዳዳሪ አቶ ስንታየሁ ለገሰ ለኢዜአ እንዳሉት፤ በዞኑ ካለፈው ዓመት ጀምሮ በመስኖ ስንዴ በስፋት እየተመረተ ነው፡፡

በዘንድሮውም የበጋ ወቅት 73 ሺህ አርሶ አደሮችን በማሳተፍ በ37 ሺህ ሄክታር መሬት ላይ በመስኖ ስንዴ እየለማ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ይህም ኢትዮጵያ ከውጭ የምታስገባውን የስንዴ ምርት በአገር ውስጥ ለመተካት የሚደረገውን ጥረት በማገዝ ረገድ ሚናው የጎላ ነው ሲሉ ተናግረዋል፡፡

የዞኑ ግብርና ጽህፈት ቤት ምክትል ኃላፊ አቶ ሙስጠፋ ሁሴን በበኩላቸው በዞኑ 400 ትራክተሮች እና 163 ኮምባይነሮች አገልግሎት እንዲሰጡ በማድረግ በኩታ ገጠም የሜካናይዝድ እርሻ ተጀምሯል ብለዋል፡፡

አርሶ አደሩ በስፋት እየተጠቀመበት የሚገኘውን ማዳበሪያ   በኮምፖስት ለመተካት እንቅስቃሴ እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል።

በአርሲ ዞን ካሉ 28 ወረዳዎች በ25ቱ በበጋ መስኖ ስንዴ እየለማ ሲሆን፤ በቀጣይ 55 ሺህ ሄክታር መሬት በመስኖ ለማልማት እንደሚሰራም ጠቁመዋል፡፡

ከኦሮሚያ ክልል ምስራቅ ወለጋ፣ ምስራቅ ሃረርጌ እና ከፊንፊኔ ልዩ ዞን የተወጣጡ ልዑካን በአርሲ ዞን በበጋ መስኖ እየለማ የሚገኘውን የስንዴ ማሳ ጎብኝተዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም