ቋንቋዎችን በማጎልበት ቁልፍ የልማት መሳሪያ አድርጎ መጠቀም ይገባል--- ሚኒስቴሩ - ኢዜአ አማርኛ
ቋንቋዎችን በማጎልበት ቁልፍ የልማት መሳሪያ አድርጎ መጠቀም ይገባል--- ሚኒስቴሩ
ሆሳዕና የካቲት 14/2014 (ኢዜአ) ቋንቋዎችን በማጎልበት ቁልፍ የልማት መሳሪያ አድርጎ መጠቀም ይገባል ሲል የባህልና ስፖርት ሚኒስቴር አስገነዘበ።
ዓለም አቀፍ በአፍ መፍቻ ቋንቋ የመናገር ቀን "ብዝሀነት ለአገራዊ መግባባት" በሚል መሪ ሀሳብ በአገር አቀፍ ደረጃ ለ12ኛ ጊዜ በዋቸሞ ዩኒቨርሲቲ ተከብሯል።
የሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ አህመድ መሀመድ እንዳሉት መንግስት በአፍ መፍቻ ቋንቋ መናገር እየጎለበተ እንዲመጣ ልዩ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ ነው።
በየዓመቱ የካቲት 14 በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚከበረው በአፍ መፍቻ ቋንቋ የመናገር ቀን በተለያዩ ኩነቶች እንዲከበር መደረጉ የትኩረቱ አንድ አካል መሆኑን ጠቅሰዋል።
ቋንቋ ለማህበራዊ ትስስር መጎልበት፣ ብዝሀነትን ለማጠናከር እንዲሁም የሰብዓዊ መብትን ለማስጠበቅ ወሳኝ በመሆኑ እንዲጎለብት መስራት እንደሚገባ ተናግረዋል።
በተለይም የአፍ መፍቻ ቋንቋዎችን በማልማት ለአገራዊ ብልጽግና መረጋገጥ ቁልፍ የልማት መሳሪያ አድርጎ መጠቀም እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
የዋቸሞ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶክተር ሀብታሙ አበበ በበኩላቸው ዩኒቨርሲቲው የአፍ መፍቻ ቋንቋዎችን ለማጎልበትና አገር በቀል እውቀቶችን ለመጠቀም ያስችል ዘንድ የተለያዩ የአገሪቱን ቋንቋዎች በአንድ ቋት የመሰነድ ሥራ እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል።
ዩኒቨርሲቲው የአካባቢውን የአፍ መፍቻ ቋንቋ ለማሳደግ እንዲረዳ የትምህርት ክፍል በመክፈት በመጀመሪያ ዲግሪ ደረጃ መምህራንን በማሰልጠን ላይ መሆኑን አመልክተዋል።
በኢትዮጵያ በርካታ የአፍ መፍቻ ቋንቋዎች ቢኖሩም በተለያዩ ምክንያቶች እንዳይጠፉና ለቀጣይ ትውልድ ለማሸጋገር በቴክኖሎጂ የታገዘ ሥራ መስራት እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
በመድረኩ ከሃዋሳ ዩኒቨርሲቲ የመጡት የስነ ልሳንና ምርምር መምህር ዶክተር ፈቀደ ምኖታ የአፍ መፍቻ ቋንቋን ማጎልበት ማህበራዊ እሴቶችን አጠናክሮ ለማስቀጠል ወሳኝ ሚና እንዳለው ተናግረዋል።
የአፍ መፍቻ ቋንቋ ተማሪዎች በቂ የሆነ እውቀት እንዲሸምቱና በዘርፉ ብቁ የተማረ የሰው ኃይል ለመፍጠር እየተሰራ መሆኑን አመልክተዋል።
የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት መስፋፋትን ተከተሎ የአፍ መፍቻ ቋንቋን ለማጎልበት ዘርፈ ብዙ ሥራዎች መከናወን መጀመራቸውን ገልጸዋል።
በአካባቢው የአፍ መፍቻ ቋንቋ ላይ የጥናትና ምርምር ሥራዎች በማከናወን ላይ መሆናቸውን የተናገሩት ደግሞ የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የባህልና ቋንቋ ጥናት ተቋም ዳይሬክተር ዶክተር ሰይድ አህመድ ናቸው።
ቋንቋዎች ለትምህርት፣ ለመገናኛ ብዙሀንና ለምርምር ጥቅም ላይ እንዲውሉ ለማድረግ ዘርፈ ብዙ ሥራ እየተከናወነ መሆኑን ተናግረዋል።
በመድረኩ የቋንቋ ፖሊሲ ይዘትና የህብረተሰብ ግንባታ እንዲሁም በአገሪቱ የምልክት ቋንቋ ላይ እየተከናወኑ ያሉ የጥናትና ምርምር ሥራዎች ቀርበው ውይይት ተደርጎባቸዋል።
የባህልና ስፖርት ሚኒስቴር ከደቡብ ክልል ባህልና ቱሪዝም ቢሮና ከዋቸሞ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር ባዘጋጀው መድረክ የተለያዩ ባለድርሻ አካላት ተሳትፈዋል።