ቀጥታ፡

የኢትዮ-ጅቡቲ የባቡር ትራንስፖርት አገልግሎት የትራንስፖርት ዘርፉን በማዘመንና በማሳደግ ጉልህ አስተዋጽኦ እያበረከተ ነው

የካቲት 15 ቀን 2014 (ኢዜአ) የኢትዮ-ጅቡቲ የባቡር ትራንስፖርት አገልግሎት በኢትዮጵያ የትራንስፖርት ዘርፉን በማዘመንና በማሳደግ ጉልህ አስተዋጽኦ እያበረከተ መሆኑን የትራንስፖርትና ሎጂስቲክ ሚኒስትሯ ዳግማዊት ሞገስ ተናገሩ።
ኢትዮ-ጅቡቲ ስታንዳርድ ጌጅ ባቡር ትራንስፖርት አክሲዮን ማህበር ከአዲስ አበባ እስከ  ድሬደዋ በሚሰጠው የትራንስፖርት አገልግሎት ተጨማሪ ጣቢያዎች መክፈቱን አብስሯል።

በመርሃ ግብሩ ላይ በመገኘት መልእክት ያስተላለፉት የትራንስፖርት ሚኒስትሯ ዳግማዊት ሞገስ፤ ድርጅቱ ከአዲስ አበባ እስከ ጅቡቲ በሚሰጠው የትራንስፖርት አገልግሎት ከዚህ ቀደም 14 ጣቢያዎች እንደነበሩት ጠቅሰው፤ አሁን ላይ ተጨማሪ አምስት ጣቢያዎችን በመክፈት የጣቢያዎቹን ቁጥር ወደ 19 ከፍ አድርጓል ብለዋል።

የኢትዮ-ጅቡቲ የባቡር ትራንስፖርት አገልግሎት በኢትዮጵያ የትራንስፖርት ዘርፉን በማዘመንና በማሳደግ ጉልህ አስተዋጽኦ እያበረከተ መሆኑን አንስተዋል።

ለተጓዦች ከሚሰጠው የጉዞ አገልግሎት ባሻገር በተለይ በኢትዮ-ጅቡቲ የእቃ ጫኝ ባቡሮች በሚሰጠው የጭነት አገልግሎት በዘርፉ ጎልቶ  ይታይ የነበረውን ክፍተትና የተጓተተ አሰራር እያቃለለ መሆኑን አንስተዋል።

የባቡር ትራንስፖርት አገልግሎትም ተጓዦች በሚፈልጉት አማራጭ አገልግሎቱን እንዲያገኙ ምቹ ሁኔታን የሚፈጥር ነው ብለዋል።

በዚህም  ከኢትዮ-ጅቡቲ  የባቡር ትራንስፖርት አገልግሎት ልምድ በመቅሰም አገልግሎቱን ወደ አፍሪካ ቀንድ ለማስፋት  በትኩረት መስራት ያስፈልጋል ነው ያሉት።

የኢትዮ-ጅቡቲ ስታንዳርድ ጌጅ ባቡር ትራንስፖርት አክሲዮን ማህበር ዋና ዳይሬክተር ኢንጂነር ጥላሁን ሳርካ፤ ጣቢያዎቹን መጨመር ያስፈለገው የአገልግሎት ተደራሽነትን ለማስፋት መሆኑን ተናግረዋል።

ተጨማሪ ጣቢያዎቹ ከአዲስ አበባ እስከ ድሬደዋ ባሉ አካባቢዎች በሚገኙ ወረዳዎችና ከተሞች የሚኖሩ ዜጎች  ምቹ የባቡር ትራንስፖርት አገልግሎት እንዲያገኙ ያስችላል ብለዋል።

ከዛሬ ጀምሮ ተጨማሪዎቹ ጣቢያዎች ለአገልግሎት ክፍት መሆናቸውን ጠቅሰው፤ የትራንስፖርት አገልግሎቱ ሁሉንም የማህበረሰብ ክፍል ያማከለ ይሆን ዘንድ የክፍያ ሥርዓቱ ዝቅተኛ እንዲሆን ተተምኗል ብለዋል።

በተጨማሪነት የተከፈቱት ጣቢያዎች አቃቂ፣ አዋሽ፣ ሙሉ፣ አፍዴምና ኤረር መሆናቸውን ያብራሩት ዋና ዳይሬክተሩ በሳምንት ሁለት ቀናት ባቡሮቹ አገልግሎቱን የሚሰጡ ይሆናል።

በኢትዮጵያ የቻይና አምባሳደር ቻዎ ቺዩዋን፤ የኢትዮጵያና የቻይና ወዳጅነት ለዘመናት የቆየና አሁንም በጠንካራ መሰረት ላይ የተገነባ መሆኑን ተናግረዋል።

የቻይና መንግስት በኢትዮጵያ በተለያዩ የመሰረተ ልማት ዝርጋታዎች በኮንስትራክሽን በኤሌክትሪክ ዝርጋታና በተለያዩ የልማት ሥራዎች ላይ እየተሳተፈ ይገኛል ብለዋል።

ይህም የሁለትዮሽ ግንኙነቱን ይበልጥ የሚያጠናክር መሆኑን ገልጸው፤ይህ ተግባር ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም አረጋግጠዋል።

በተለይም የመንገድ ዝርጋታ ከኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታው በዘለለ ከጎረቤት አገራትና በአገሪቱ ያሉ ከተሞችንና ህዝቦችን በማስተሳሰር የላቀ ጠቀሜታ እንዳለው አንስተዋል።

በኢትዮ-ጅቡቲ የትራንስፖርት አገልግሎት የታየውም ይኸው ነው ያሉት አምባሳደሩ፤ የትራንስፖርት አገልግሎት አንዱ የሰላም መፍጠሪያ መንገድ ነው ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም