ቀጥታ፡

የተወሰኑ ግለሰቦች ክስ በመቋረጡ ምክንያት ኢትዮጵያ ባለፈው አንድ ወር በርካታ ጥቅሞችን አግኝታለች

የካቲት 15 ቀን 2014 (ኢዜአ) ''የተወሰኑ ግለሰቦች ክስ በመቋረጡ ምክንያት ኢትዮጵያ ባለፈው አንድ ወር በርካታ ጥቅሞችን አግኝታለች'' ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ ተናገሩ፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 3ኛ አስቸኳያ ስብሰባ በመገኘት ከምክር ቤቱ አባላት ለተነሱ ጥያቄዎች ምላሽ ሰጥተዋል፡፡

ከተነሱት ጥያቄዎች መካከል አንዱ "መንግስት አቶ ስብሃት ነጋን ጨምሮ የተወሰኑ ግለሰቦችን ክስ ያቋረጠው ከሕግ አግባብና ሕገ መንግሥቱን በሚጣረስ መልኩ ነው" የሚል ነው።

በመሆኑም ክስ የማቋረጥ ውሳኔው ከኃቅ፣ ከፍትህና ከሞራል ሕጋዊነት አንጻር ተመርምሮ እንዲሻር ጥያቄ ቀርቧል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በምላሻቸው "ከዚህ በፊት የምክር ቤቱ አባላት ጥያቄ እንዴት እስረኛ አይፈታም የሚል ነበር፤ አሁን ይህ ሁኔታ መቀየሩ በጎ ጅምር ነው'' ብለዋል።

በመሆኑም የክስ ማቋረጡ ውሳኔ ከህግ መንግስቱም ሆነ በምክር ቤቱ ከጸደቁ የህግ አዋጆች ጋር የማይጣረስና እንደ አገር ትልቅ ጥቅም የተገኘበት ነው ብለዋል።

እንደ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ገለጻ፤ ኢትዮጵያ የተወሰኑ ግለሰቦችን ክስ በማቋረጧ ምክንያት ባለፈው አንድ ወር በርካታ ጥቅሞችን አግኝታለች።

የክስ ማቋረጥ ሂደቱ ዘላቂ ሰላም ማምጣትን፤ የግለሰቦችን ሁለንተናዊ ሁኔታ እንዲሁም እንደ አገር የተገኘውን ድል ማጽናትን ታሳቢ ያደረጉ ስለመሆኑም ነው ያብራሩት፡፡

የክስ ማቋረጡ ውሳኔው የኢትዮጵያዊያን አሸናፊነት እና  የሞራል ልዕልና ምን ያህል ትልቅ እንደሆነ የታየበት ነው ብለዋል።

አሸናፊዎች ሁሌም ቢሆን ቆም ብለው የሚመለከቱና ወደ ፊት የሚራመዱ ናቸው ሲሉም ነው ጠቅላይ ሚኒስትሩ የተናገሩት፡፡

በሌላ በኩል የኢትዮጵያ መንግስት ከአሸባሪው ሕወሓት ጋር እየተደራደረ ስለመሆኑ የተጠየቁት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ "እስካሁን የተደረገ ድርድር የለም"  ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል፡፡

ነገር ግን መንግስት በኢትዮጵያ የሚያጋጥሙ ችግሮችን በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት ሁሌም ዝግጁ መሆኑን አብራርተዋል፡፡

"ድርድር ኢትዮጵያን ተጠቃሚ የሚያደርግ አማራጭ መፍትሄ ከሆነ የማይደረግበት ምክንያት የለም'' ሲሉም ነው የተናገሩት፡፡

''ድርድር እርቅ አይደለም፣ ትርፍ ግን ይገኝበታል'' ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ''ለኢትዮጵያ ሉዓላዊነትና ጥቅም ያለንን አቋም በጦርነቱ ወቅት በግልጽ ማሳየታቸን ይታወቃል'' በማለት ገልጸዋል።

''አሁንም ለኢትዮጵያ አንድነት የሚከፈለውን መሰዋዕትነት እንከፍላለን፤ የሰላም አማራጭ ካለ እሱን መመልከት ተገቢ ነው'' ብለዋል።

ሌሎች የፖለቲካ ድርጅቶችም ይህን እድል ለማባላሸት ከመጣደፍ ይልቅ አማራጭ ሁኔታዎችን ማዬት ቢችሉ መልካም መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትሩ አሳስበዋል።

''ሂደቱ ህግ አለው፤ መርህ አለው፤ በዛ መሰረት መሔድ ያለበት ነገር ካለ ተጨማሪ ማብረሪያ ሊሰጥ ይችላል" ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትሩ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም