ቀጥታ፡

አገራት ዜጎቻቸውን በአፍ መፍቻ ቋንቋ ማስተማርን ቁልፍ አጀንዳ አድርገው ሊሰሩ ይገባል

አዲስ አበባ፣ የካቲት 15/2014 (ኢዜአ)  አገራት ዜጎቻቸውን በአፍ መፍቻ ቋንቋ ማስተማርን ቁልፍ አጀንዳ አድርገው ሊሰሩ እንደሚገባ ተመላከተ።

ዓለም አቀፉ የአፍ መፍቻ ቋንቋ ቀን በተባበሩት መንግስታት ድርጅት በአፍሪካ ኢኮኖሚ ኮሚሽን (ECA) አዳራሽ ተከብሯል።      

ቀኑ በኢትዮጵያ የባንግላዲሽ ኢምባሲ ከዩኔስኮ ጋር በመሆን ባዘጋጀው መርሃ ግብር ላይ የተለያዩ አገራት ኢምባሲዎች፣ ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።     

የባህልና ስፖርት ሚኒስትር ደኤታው አምባሳደር መስፍን ቸርነት፤ ቋንቋ ሰዎች ልዩ ቦታ የሚሰጡትና ራሳቸውን የሚገልጹበት ትልቅ መሳሪያ ነው ብለዋል።   

ቋንቋ የዜጎች ማንነት መገለጫ መሆኑን ያስታወሱት ሚኒስትር ዴኤታው በአንድ አገር ፖለቲካ ምህዳር ውስጥ ትኩረት የሚሰጠው ቁልፍ አጀንዳ ሊሆን ይገባል ብለዋል።     

በአንድ አገር ውስጥ በአፍ መፍቻ ቋንቋ ትምህርት መስጠት እንዲሁም የፖለቲካ ተሳትፎን ማሳደግ ወሳኝ መሆኑንም አስምረውበታል።    

ቋንቋ በአንድ አገር ወስጥ አገር በቀል እውቀቶችን ዘላቂነት ባለው መንገድ ከትውልድ ወደ ትውልድ ማስተላለፊያ መንገድ ነው።   

በመድረኩ ላይ የኢትዮጵያን ተሞክሮ ሲያብራሩም አገሪቷ ተማሪዎች በአፍ መፍቻ ቋንቋቸው እንዲማሩ በመደረጉ ውጤታማ መሆን ችለዋል ሲሉም ጠቅሰዋል።   

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የአፍሪካ ኢኮኖሚ ኮሚሽን ተወካይ ላውራ ፓኢዝ፤ ቁጥራቸው ቀላል የማይባል አገራት ዜጎቻቸውን በአፍ መፍቻ ቋንቋቸው እያስተማሩ አለመሆኑን ጠቅሰዋል።

ዘላቂነት ያለው ማህበረሰብ ለመገንባት ቋንቋ ወሳኝ መሆን በመገንዘብ አገራት ትኩረት ሊሰጡበት እንደሚገባም ተናግረዋል።    

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ጠቅላላ ጉባኤ ባሳለፈው ውሳኔ መሰረት ሁሉም አገራት አገር በቀል የሆነውን ቋንቋቸውን እንዲጠብቁና እንዲያለሙ ደንግጓል።     

በመሆኑም አገራት የውሳኔውን ተግባራዊነት ለማረጋገጥ የሚጠበቅባቸውን ሚና መጫወት አለባቸው ብለዋል።     

ዓለም አቀፉ የአፍ መፍቻ ቋንቋ ቀን በተባበሩት መንግስታት ድርጅት እንዲከበር ከታወጀበት እ.ኤ.አ ከ2000 ጀምሮ እየተከበረ ይገኛል።  

የቀኑ መከበር ዋና ዓላማም ቋንቋዎች ተጠብቀው እንዲቆዩ አጽንኦት ለመስጠት መሆኑ ታውቋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም