አገራዊ ምክክሩ እየተሸጋገሩ የመጡ ቁርሾዎችን ለማከምና የተሻለ ነገን ለመገንባት የጎላ ሚና አለው

27

የካቲት 15 ቀን 2014 (ኢዜአ) አገራዊ ምክክሩ እየተሸጋገሩ የመጡ ቁርሾዎችን ለማከምና የተሻለ ነገን ለመገንባት ሚናው የጎላ ነው ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ ተናገሩ፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 3ኛው አስቸኳይ ስብሰባ ላይ በመገኘት ከምክር ቤቱ አባላት ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች ምላሽ ሰጥተዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማብራሪያቸው አሁን ላይ ለነገ አስበን እየገነባነው ያለው ነገር አገርና ትውልድን ታሳቢ ያደረገ ከፓርቲም ከስልጣንም በላይ በመሆኑ ትልቅ ትርጉም አለው ብለዋል።

በመሆኑም አገራዊ ምክክሩ አካታች እና አሳታፊ መሆን እንዳለበት ጠቅሰው፤ ምክክሩ ቅቡልነት ያለው ውጤት ማስመዝገብ ያስችላል ነው ያሉት፡፡

በፖለቲካና ሃሳብ ልዩነቶቻችን ምክንያት መገዳደልና መባላት ማቆም አለብን ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ከዚህ አኳያ አገራዊ ምክክሩ ይዘናቸው የመጣናቸውን ቁርሾዎች ለማከምና የተሻለ ነገን ለመገንባት የጎላ ሚና አለው ብለዋል።

በመሆኑም የፖለቲካ ፓርቲዎችን ጨምሮ ሁሉም ባለድርሻ አካላት አገራዊ ምክክሩ ይዞት የመጣውን እድል ሊጠቀሙ እንደሚገባ አስገንዝበዋል፡፡

የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አገራዊ የምክክር ኮሚሽንን በማቋቋምና አባላትን በመሾም ረገድ ላበረከቱት አስተዋጽኦም ምስጋና አቅርበዋል፡፡

አገራዊ ምክክሩ ሁሉንም አካታች እና አሳታፊ እንዲያደርግ በጥንቃቄ መሰራት እንደሚገባም አስገንዝበዋል፡፡

ኢትዮጵያን እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ‼

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም