ቀጥታ፡

ግንቦት 20 ብሔራዊ መግባባትና ዴሞክራሲያዊ አንድነትን በሚያጠናክሩ ውይይቶች ይከበራል ተባለ

አዲስ አበባ ግንቦት 10/2010 የግንቦት 20 የድል በዓል ብሔራዊ መግባባትና ዴሞክራሲያዊ አንድነትን በሚያጠናክሩ ውይይቶች እንደሚከበር የአዲስ አበባ ከተማ ኮሙኒኬሽን ቢሮ አስታወቀ። የቢሮው ኃላፊ ወይዘሮ ዳግማዊት ሞገስ በዓሉን አስመልክተው ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ እንዳሉት በዓሉ ሲከበር በፌዴራሊዝም ስርዓት አተገባበር ላይ የሚታዩ ጉድለቶችን ለማጥበብ የሚያስችሉ ውይይቶች ይካሄዳሉ። በተለይም የከተማው ነዋሪ ስርዓቱን በባለቤትነት መንፈስ እንዲጠብቅና ወጣቱ የስርዓቱ ተቆርቋሪ እንዲሆን የሚያስችሉ ቅድመ ዝግጅቶች መካሄዳቸውን አብራርተዋል። ግንቦት 20 የኢትዮጵያ ህዝቦች የጋራ የድል ውጤትና አዲሲቷን ኢትዮጵያ ለመመስረት መሰረት የጣለ ነው ያሉት ወይዘሮ ዳግማዊት ህብረተሰቡ በንቃት እንዲሳተፍ ጥሪ አቅርበዋል። በበዓሉም ትውልዱ የከተማውን ሰላም ለማስጠበቅና የተገኘውን መልካም ነገር ለማስቀጠል ቃል የሚገባበት ነው ብለዋል። ውይይቶቹ ከነገ ጀምሮ በሁሉም ወረዳዎች መካሄድ እንደሚጀምሩም ገልፀዋል፡፡ ከዚህ ባሻገር የከተማዋን ነዋሪና ተሰሚነት ያላቸውን ሰዎች በማስተባበር ግንቦት 25 ቀን 2010 ዓም የጽዳት ዘመቻ እንደሚካሄድ የቢሮ ኃላፊዋ ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም