መንግስት በቀጣይ ጊዜያት በአምስት ጉዳዮች ላይ አተኩሮ ይሰራል

66

የካቲት 15 ቀን 2014 (ኢዜአ)  መንግስት በቀጣይ ጊዜያት በአምስት ጉዳዮች ላይ አተኩሮ ይሰራል

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ በኢትዮጵያ ወቅታዊ  ሀገራዊ ጉዳዮች  ላይ ከህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች ማብራሪያ ሰጥተዋል።

መንግስት በቀጣይ ጊዜያት በመከላከያ፣ በውይይት፣ በዲሞክራሲ፣ በልማትና በዲፕሎማሲ ላይ አተኩሮ እንደሚሰራ ጠቅላይ ሚኒትር ዐቢይ ተናግረዋል፡፡

ሀገሪቱን ወደ ተሻለ ደረጃ ለማሸጋገርና ብሄራዊ ጥቅምን በዘላቂነት ለማረጋገጥ ሉዓላዊነትንና ሰላምን መሰረት ያደረገ የመከላከል ተግባር እንደሚከናወንም አስረድተዋል፡፡

መንግስት ከፖለቲካ ፓርቲዎች፣ ተቺዎችና ከሀገራት ጋር ዘላቂና ችግር ፈቺ ውይይት በማድረግ የጋራ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ እንደሚሰራም ተናግረዋል፡፡

በሀገሪቱ ሁለንተናዊ የዲሞክራሲ ስርአትን በማረጋገጥ ህብረተሰቡን በንቃት የሚያገለግሉ የፍትህ አካላትንና አገልግሎት ሰጪ ተቋማትን ለመገንባት እንደሚሰራም ጠቁመዋል፡፡

በሀገሪቱ የተጀመሩ ሁለንተናዊ የልማት ስራዎችን በማስፋፋት ህዝቡን ተጠቃሚ ማድረግ የመንግስት የትኩረት አቅጣጫ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡

ልማትን በማረጋገጥ ብልጽግናን እውን ማድረግ ህልም ብቻ ሳይሆን ግዴታችንም ጭምር ነው ብለዋል፡፡

ከሀገራት ጋር ያለውን የዲፕሎማሲ ግንኙነት በማጠናከርና ልዩነቶችን በመነጋገር በመፍታት ዘላቂና በጋራ ተጠቃሚነት ላይ የተመሰረተ አጋርነት ለመፍጠር መንግስት አበክሮ ይሰራል ብለዋል፡፡

የዲፕሎማሲ ግንኙነትን በማጠናከር ልዩነትን መፍታት ከተቻለ ሀገራት ልማታችንንና ራዕያችንን እንድናሳካ ድጋፍ እንዲሰጡን ማድረግ እንችላለን በማለት ተናግረዋል ፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም