በኢትዮጵያ ባለፉት ስድስት ወራት ከውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት 1 ነጥብ 6 ቢሊየን ዶላር ኢንቨስት ተገኝቷል

40

አዲስ አበባ፣ የካቲት 15/2014 (ኢዜአ)  በኢትዮጵያ ባለፉት ስድስት ወራት ውስጥ 1 ነጥብ 6 ቢሊየን ዶላር ኢንቨስትመንት መገኘቱን ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ ገለጹ፡፡

የኢንቨስትመንት ክንውኑ ከአምናው ተመሳሳይ ወራት ጋር ሲነፃፀር 23 በመቶ እድገት አሳይቷል።

የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እያካሄደ ባለው 3ኛ አስቸኳይ ስብሰባ ከምክር ቤት አባላት ለተነሱላቸው የተለያዩ ጥያቄዎች ጠቅላይ ሚኒስትሩ ምላሽና ማብራሪያ ሰጥተዋል።

በማብራሪያቸውም በኢትዮጵያ የንግድ እንቅስቃሴ ላይ ለሚሳተፉ ከ200 ሺህ በላይ የንግዱ ተዋንያን አዳዲስ የንግድ ፈቃድ መሰጠቱን ገልጸዋል፡፡

የኮቪድ-19 ወረርሽኝ የዓለምን ኢኮኖሚ ሦስት በመቶ ቀንሷል፤ በዚህም የዓለም የሸቀጦች ዋጋ በጣም ጨምሯል፤ ኢትዮጵያም የዚሁ ችግር ተጋሪ መሆኗን ጠቁመዋል፡፡

ከዚህም ባለፈ በኢትዮጵያ የተከሰተው የጸጥታ ችግር የአገሪቱን የንግድና ኢንቨስትመንት እንቅስቃሴ አሉታዊ ተጽዕኖ አሳድሮበታል ብለዋል።

"አንዳንድ አገሮች በግራ እጃቸው በኢትዮጵያ ሰላም የለም እያሉ በቀኝ እጃቸው መዋዕለ ንዋያቸውን እያፈሰሱ ነው" ብለዋል።

በኢትዮጵያ ባለፉት ስድስት ወራት ከውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት 1 ነጥብ 6 ቢሊየን ዶላር ተጨማሪ መዋዕለ ንዋይ ፈሰስ መደረጉንም ገልጸዋል፡፡

በተለይ የኢነርጂ ዘርፉ ብቻ በርካታ ኢንቨስተሮችን የመሳብ አቅም እንዳለው ጠቅሰው ከዚህም ባሻገር የንግዱን ዘርፍ ተዋንያን በማሳደግ ከፍተኛ ለውጥ መመዝገቡን ገልጸው ዘንድሮ ከ200 ሺህ በላይ አዳዲስ የንግድ ፈቃድ ተሰጥቷል ብለዋል፡፡

በጦርነቱ እንቅስቃሴ ያቆሙ ቦታዎች እንዳሉ ሆነው ከ845 ሺህ በላይ ለሚሆኑ የንግዱ ተዋንያን የንግድ ፈቃድ መታደሱን ገልጸዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም