የእገታ ወንጀል የፈጸመ ግለሰብ በ12 ዓመት ፅኑ እስራት ተቀጣ

ጎንደር፣ የካቲት 15/2014 (ኢዜአ) በማዕከላዊ ጎንደር ዞን የ10 ዓመቱን ታዳጊ ህጻን በማገት ወንጀል ጥፋተኛ የተባለ ግለሰብ በ12 ዓመት ጽኑ እስራት መቀጣቱን የዞኑ ከፍተኛ ፍርድ ቤት አስታወቀ፡፡

የፍርድ ቤቱ የህዝብ ግንኙነትና ኮሙኒኬሽን ባለሙያ ወይዘሮ ማስተዋል ወርቁ ለኢዜአ እንደገለፁት የእስራት ቅጣቱ የተላለፈው በማዕከላዊ አርማጭሆ ወረዳ ነዋሪ በሆነው ዮሐንስ አሸተ መኮንን በተባለ ግለሰብ ላይ ነው።

ግለሰቡ በወረዳው ፉጨና ቀበሌ ልዩ ስሙ "ደላጎ" እየተባለ በሚጠራ ቦታ ከብት ይጠበቅ የነበረን የ10 ዓመት ታዳጊ ህጻን በጨርቅ አፍኖ ወደ ጫካ ወስዶ እገታ በመፈፀም ወንጀል ጥፋተኛ ተብሏል።

ህጻኑን ካገተ በኋላም ቤተሰቦቹን 70ሺህ ብር አምጡ፤ ካላመጣችሁ እገድለዋለሁ በሚል እንግልት መፈፀሙን ወይዘሮ ማስተዋል ገልፀዋል።

እንደ ባለሙያዋ ገለጻ ግለሰቡ በስልክ ያቀረበውን የገንዘብ ጥያቄ የህጻኑ ቤተሰቦች ባለመቀበላቸው ለ6 ቀናት ጫካ ውስጥ አግቶ በማቆየት መልቀቁን በዐቃቤ ህግ የሰው ምስክሮች ተረጋግጧል።

ጉዳዩን የተመለከተው የዞኑ ከፍተኛ ፍርድ ቤት የተከሳሽን የእምነት ክህደት ቃል ተቀብሏል።

"ግለሰቡ የክስ ተቃውሞ የለኝም፤ የወንጀል ድርጊቱን አልፈፀምኩም፤ ጥፋተኛ አይደለሁም፤ በማለት መንግስት በመደበለት ተከላካይ ጠበቃ በኩል ክዶ ተከራክሯል" ብለዋል።

ፍርድ ቤቱ የግራ ቀኙን ማስረጃ ካደመጠ በኋላ መዝገቡን መርምሮ ተከሳሽ በወንጀለኛ መቅጫ ስነ ስርአት ህግ ቁጥር 149/1 መሰረት የጥፋተኝነት ውሳኔ ማሳለፉን ባለሙያዋ ገልፀዋል።

"ተከሳሹ ወንጀሉን በአፍቅሮተ ንዋይና በስግብግብነት የፈፀመው መሆኑን በማክበጃነት እንዲሁም የቤተሰብ አስተዳዳሪና ከዚህ ቀደም የወንጀል ሪከርድ የሌለበት መሆኑን በቅጣት ማቅለያነት በፍርድ ቤቱ ተይዞለታል" ሲሉ አብራርተዋል።

ፍርድ ቤቱ ተከሳሹን ያርማል፤ ሌላውንም ማህበረሰብ ያስተምራል በማለት በ12 ዓመት ጽኑ እስራት እንዲቀጣ መወሰኑን ባለሙያዋ አስታውቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም