የአገር ውስጥ ኢንዳስትሪዎች የማምረት አቅምን 46 በመቶ ማድረስ ተችሏል

25

አዲስ አበባ፣ የካቲት 15/2014 (ኢዜአ) ባለፉት ስድስት ወራት የአገር ውስጥ ኢንዳስትሪዎችን የማምረት አቅም 50 በመቶ ለማድረስ ታቅዶ 46 በመቶ ማድረስ መቻሉን ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ ተናገሩ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ፤ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እያካሄደ ባለው 3ኛ አስቸኳይ ስብሰባ ከምክር ቤት አባላት ለተነሱላቸው የተለያዩ ጥያቄዎች ምላሽና ማብራሪያ ሰጥተዋል።

ከተነሱት ጥያቄዎች መካከል በኢንዳስትሪና በቱሪዝም ዘርፍ የመንግስት ስራ አፈጻጸም ምን ላይ እንዳለ እንዲብራራ ተጠይቋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በምላሻቸውም የአገር ውስጥ ኢንዳስትሪዎች የማምራት አቅማቸው 50 በመቶ ማድረስ ታቅዶ እንደነበር አንስተዋል።

እቅዱ ሙሉ ለሙሉ በተለያዩ ምክንያቶች ባይሳካም 46 በመቶ ማሳካት ተችሏል ብለዋል።

በቀጣይ ከ70 እስከ 80 በመቶ ማድረስ ቢቻል አገራዊ ጠቀሜታው የጎላ እንደሚሆን አስረድተዋል።

የኢንዳስትሪ ፓርኮች አጠቃላይ ሁኔታን አስመልክተውም በፓርኮች ውስጥ ካሉ 177 ሼዶች መካከል 104 ሼዶች ሙሉ በሙሉ ስራ ሲጀምሩ 158 ሼዶች ደግሞ በግል ባለሃብቶች ተይዘው ወደ ስራ የገቡና ወደ ስራ ለመግባት በሂደት ላይ ይገኛሉ ብለዋል።

ባለፉት ጥቂት ዓመታት የተጀመሩትን ፓርኮች ከማጠናቀቅ አንጻር የተሳካ ስራ እንደተሰራም ጠቅላይ ሚኒስትሩ አንስተዋል።

ፓርኮቹ የሚያመርቱት አልባሳት ለውጪ ንግድ ብቻ ሳይሆን ለአገር ውስጥም ጥቅማቸው የላቀ መሆኑን አስረድተዋል።

የጸጥታ ሃይሎች ዩኒፎርም በአብዛኛው ከውጪ የሚገባ መሆኑን ጠቅሰው ይህን መቀነስ በአገር ውስጥ ምርት በመተካት ወጪ ማስቀረት ይገባል ነው ያሉት።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማብራሪያቸው ባለፉት ስድስት ወራት በአገልግሎት ዘርፍም የተሻለ ስራ ተሰርተዋል ብለዋል።

በኮቪድ 19 ወረርሺኝ ምክንያት የተቀዛቀዘውን ቱሪዝም ለማካካስ የመዳረሻ ቦታ የመገንባት ስራ በስፋት መሰራቱን አንስተዋል።

ከዚህ ባለፈም የአገር ውስጥ ቱሪዝምን በማሳደግ ረገድ በተለይም ዳያስፖራው የተደረገለትን ጥሪ ተከትሎ ወደ አገሩ መምጣቱ የቱሪዝም ዘርፉን በሚገባ አነቃቅቷል፣ ምስጋናም ያስፈልጋል ብለዋል።

በቀጣይም ዳያስፖራው ''ከእኛ ጋር ኢድን ቢያከብር መልካምና ጠቃሚ ይሆናል'' በማለት በመላው ዓለም ለሚገኙ ለኢድ እንዲገኙ ጥሪ አቅርበዋል።

የባለፈው የዳያስፖራ ጉዞ ኢትዮጵያ ሰላምና ተስፋ ያላት አገር መሆኗን በአግባቡ አሳይቷል፣ 35ኛው የአፍሪካ ሕብረት የመሪዎች ጉባኤውም ለቱሪዝሙ መነቃቃት መልካም አጋጣሚ ፈጥሯል ብለዋል።

ከዚህ ጎን ለጎን በዚህ ሂደት የኢትዮጵያ የአየር መንገድ ትልቅ እምርታ አሳይቷል፣ የቱሪዝም ዘርፉን በማሳደግ ትልቅ ድርሻ ነበረው ሲሉም አንስተዋል።

ከጥቂት ወራት በኋላም በዓለም አቀፍ ደረጃ በሚመጥን መልኩ በጎርጎራ የተሰራው ስራ፣ ኮይሻና ወንጪ ላይ እየተሰራ ያለው ስራ ትልቅ የቱሪዝም አቅም የሚፈጥር መሆኑን ጠቅሰዋል።

በቀጣይም በትላልቅ ሃይቆች አካባቢ ትላልቅ የቱሪዝም ከተሞች የመገንባት እቅድ መኖሩን ጠቅላይ ሚኒስትሩ አመላክተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም