ባለፉት ስድስት ወራት አንድ ቢሊዮን ዶላር የሚጠጋ ገንዘብ ይወጣባቸው የነበሩ የገቢ ምርቶችን በአገር ውስጥ ምርት መተካት ተችሏል - ኢዜአ አማርኛ
ባለፉት ስድስት ወራት አንድ ቢሊዮን ዶላር የሚጠጋ ገንዘብ ይወጣባቸው የነበሩ የገቢ ምርቶችን በአገር ውስጥ ምርት መተካት ተችሏል

አዲስ አበባ፣ የካቲት 15/2014 (ኢዜአ) ባለፉት ስድስት ወራት አንድ ቢሊዮን ዶላር የሚጠጋ ገንዘብ ይወጣባቸው የነበሩ የገቢ ምርቶችን በአገር ውስጥ ምርት መተካት መቻሉን ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ ተናገሩ፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህን ያሉት ከህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች በሰጡት ምላሽና ማብራሪያ ነው፡፡
በኢትዮጵያ ባላፉት ስድስት ወራት የውጪ ንግድ 25 በመቶ ማደጉን ጠቅሰው፤ በዚህም 1 ነጥብ 9 ቢሊዮን ዶላር የሚጠጋ ገቢ ማግኘት መቻሉን ተናግረዋል፡፡
በበጀት ዓመቱ በአጠቃላይ ከወጪ ንግድ 4 ቢሊዮን ዶላር ገቢ ለማግኘት እንደሚሰራም ነው የጠቆሙት፡፡
ይሁንና በኢትዮጵያ ከተፈጠረው ድርቅና ሌሎች ሰብዓዊ ቀውሶች አንጻር የምግብ ሸቀጦች፣ የነዳጅና ሌሎች ምርቶች ፍላጎት በመጨመሩ የገቢ ምርት ከፍ ማለቱን አውስተዋል፡፡
በዚህም የገቢ ምርት 25 በመቶ ማደጉን ጠቅሰው፤ ይህም በንግድ ሚዛን ምጣኔ ላይ የራሱ አሉታዊ ተጽእኖ ነበረው ነው ያሉት፡፡
የድንጋይ ከሰልን ጨምሮ በርካታ የገቢ ምርቶችን በአገር ውስጥ በመተካት ረገድ አበረታች ስራ መከናወኑንም ጠቅላይ ሚኒስትሩ አብራርተዋል።
በዚህም ባለፉት ስድስት ወራት አንድ ቢሊዮን ዶላር የሚጠጋ ገንዘብ ይወጣባቸው የነበሩ የገቢ ምርቶችን በአገር ውስጥ ምርት መተካት ተችሏል ነው ያሉት።
የባንኮች ተቀማጭ ሃብትም ወደ ሁለት ትሪሊዮን ብር ከፍ ማለቱን አክለዋል፡፡
በዚህም ባንኮች ባለፉት ስድስት ወራት 147 ቢሊዮን ብር ብድር የሰጡ ሲሆን፤ ከዚህም ውስጥ ለግብርና ሴክተር የተሰጠው 27 ቢሊዮን ብር ብቻ መሆኑንም ነው ያብራሩት፡፡
በመሆኑም ለግብርና ሴክተር የሚሰጠው ብድር ሊጨምር እንደሚገባም አስገንዝበዋል፡፡
በዘንድሮው በጋ 600 ሺህ ሄክታር መሬት በስንዴ ዘር መሸፈኑን ጠቅሰው 25 ሚሊዮን ኩንታል ስንዴ ይገኛል ተብሎ እንደሚገመትም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጠቁመዋል።