ቀጥታ፡

የጤና ሳይንስ ኮሌጆች የሰው ኃይል ልማትን ለማበልጸግ በትኩረት መስራት ይጠበቅባቸዋል

አዲስ አበባ ነሀሴ 26/2010 በጤና ተቋማት የሚሰጠውን አገልግሎት ጥራት ለማስጠበቅና ተደራሽነት ለማሳደግ የጤና ሳይንስ ኮሌጆች የሰው ኃይል ልማትን ለማበልጸግ በትኩረት መስራት እንደሚጠበቅባቸው ተገለጸ። ዩኒቨርሳል የጤና ሳይንስ ኮሌጅ በ2010 ዓ.ም በቀንና በማታ በዲግሪና በደረጃ አራት መርሃ ግብር ያሰለጠናቸውን 200 የጤና ባለሙያዎች ዛሬ አስመርቋል። ኮሌጁ የጤና ባለሙያዎችን ሲያስመርቅ ዘንድሮ ለ15ተኛ ጊዜ ነው። ከተመራቂዎቹ ውስጥ በመጀመሪያ ዲግሪ መርሃ ግብር 125 በነርሲንግ፣ 32 በፋርማሲ፣ 43 በጤና መኮንን ሲሆን በዲፕሎማ ደረጃ አራት 12 የክሊኒካል ነርሲንግ እና  8 የፋርማሲ  ቴክኒሻን የጤና ባለሙያዎች ተመርቀዋል። የኮሌጁ ባለቤትና ፕሬዚዳንት ወይዘሮ የኔህት አስፋ በምርቃ ሥነ ሥርዓት ወቅት እንደገለጹት፤ መንግስት በጤና ተቋማት የአገልግሎት ጥራትን ለማስጠበቅና ተደራሽነት ለማሳደግ ለሚሰራው ሥራ ውጤታማነት የጤና ኮሌጆች በሰው ኃይል ልማት የሚሰሩት ሥራ ወሳኝነት አለው። የጤና አገልግሎትን ጥራት ለማስጠበቅና ለህብረተሰቡም ተደራሽ ለማድረግ የጤና ኮሌጆች ሚና የጎላ በመሆኑ በዘርፉ የሚሰሩ የጤና ሳይንስ ተቋማት በትኩረት መስራት አለባቸው ብለዋል። የትምህርት ጥራቱ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተሻለ  መምጣቱን የገለጹት ፕሬዚዳንቷ በተለይም በጤናው ዘርፍ  ስልጠና እየሰጡ ያሉ ኮሌጆች ቁጥር እየጨመረ መምጣቱን ገልፀዋል። ሙያው  ከሰው ልጅ የእለት ተእለት ህይወት ጋር ያለው ትስስር ጠንካራ በመሆኑ ተመራቂ የጤና ባለሙያዎች የወሰዱትን የባለሙያነት ማረጋገጫ በከፍተኛ የኃላፊነት ስሜትና ሥራው የሚጠይቀውን መስዋዕትነት በመክፈል ለአገርና ወገን የሚጠቅም ስራ መስራት እንዳለባቸውም  ገልጸዋል። በመሆኑም ተመራቂዎች ከኮሌጁ ያገኙትን እውቀትና ክህሎት በማስፋት በጥሩ ስነ-ምግባር በመታነጽ ህብረተሰቡን  በቅንነት በማገልገል ኮሌጁ  የሰጣቸውን  አደራ እንዲወጡ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል። ተመራቂ ተማሪዎች በበኩላቸው የጤና አገልግሎትን ጥራት ለማስጠበቅ ከትምህርት ቤት የቀሰሙትን እውቀት በመጠቀም ህብረተሰባቸውን በታማኝነት ለማገልገል እንደሚጠቀሙበት ተናግረዋል። ዩኒቨርሳል የጤና ሳይንስ ኮሌጅ በ15 ዓመት ቆይታው በተለያዩ የጤና ዘርፎች ከ6ሺህ በላይ ተማሪዎችን አስመርቋል።        
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም