ቀጥታ፡

ግድቡ ሃይል ማመንጨት መጀመሩ የተከፈቱብንን ጦርነቶች ያሸነፍንበት ዳግማዊ አድዋችን ነው

የካቲት 14 ቀን 2014 (ኢዜአ) ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ሃይል ማመንጨት መጀመሩ ኢትዮጵያ ግድቡን እንዳትገነባ የተከፈቱባትን ጦርነቶች በማሸነፍ ለአፍሪካና ሌሎች ጥቁር ህዝቦች ተምሳሌት የሆነችበት ዳግማዊ አድዋ ነው ሲሉ ኢዜአ ያገናገራቸው የዳያስፖራ ምክር ቤቶች አመራሮች ተናገሩ።

የምክር ቤቶቹ አመራሮቹ ግድቡ የደረሰበት ሃይል የማመንጨት ደረጃ ለኢትዮጵያ አዲስ ምዕራፍ የከፈተና መላ ኢትዮጵያውያንን ያኮራ ነው ብለዋል።

ግድቡ ሃይል ማመንጨት በመጀመሩ በውጭና በሀገር ውስጥ ያሉ ኢትዮጵያውያን ደስታቸውን እየገለጹ ይገኛሉ።

 “በአድዋ በዓል ዋዜማ ዳግማዊ አድዋችን ኃይል በማመንጨቱ ተደስትናል” ያሉት የኢትዮጵያ የዳያስፖራ የተግባር ምክር ቤት ሊቀመንበር አቶ አለባቸው ደሳለኝ፤ የኢትዮጵያ የልማት ጀግኖች ፍሬ በማፍራቱ ኮርተናል ብለዋል።

ኢትዮጵያ ግድቡን ስትገነባ ከተለያዩ ሀገራት ሲደርስባት የነበረውን የዲፕሎማሲና የገንዘብ ክልከላ ጫና ተቋቁማ ዳግማዊ አድዋን በማስመዝገቧ ኮርተናል ነው ያሉት።

ኢትዮጵያውያንም ወራሪ ሃይል ሀገር ሊወርር በመጣ ጊዜ በአንድነት ያሳዩትን ሀገራዊ ጀብዱ በግድቡ ግንባታ በመድገም ለዓለም ማሳየት ችለዋል ብለዋል።

የኢትዮጵያ አሜሪካውያን ዜጎች ምክር ቤት ሊቀመንበር ዲያቆን ዮሴፍ ተፈሪ በበኩላቸው የግድቡ ሃይል ማመንጨት መጀመር ለኢትዮጵያ አዲስ ምዕራፍ መክፈቱን አብራርተዋል።

የኢትዮ አሜሪካውያን የዕድገት ምክር ቤት ሊቀመንበር አቶ ነቢዩ አስፋው ዓባይ ለሀገራችን ብርሃንና ብልፅግና መሰረት ሆኖ የማየት ምኞታችን በመሳካቱ በመላው ዓለም ያለን ዳያስፖራዎች ተደስተናል ነው ያሉት።

ግድቡ ሃይል ማመንጨት የጀመረበት ቀን የኢትዮጵያ የህዳሴ ቀን ነው ያሉት አቶ ነቢዩ፥ ኢትዮጵያም ዳግም በህዳሴ ግድቡ በመወለዷ አዲስ ምዕራፍ መከፈቱን ተናግረዋል።

ዲያቆን ዮሴፍ በበኩላቸው ከግዙፉ ግድብ የሚኘው የኤሌክትሪክ ሃይል ኢትዮጵያን ወደ ብርሃን የሚያሸጋግርና መካከለኛ ገቢ ካላቸው ሀገራት ተርታ ለመሰለፍ መሰረት የሚጥል ነው ብለዋል።

“ኢትዮጵያውያን የማይቻልና የማይፈም ይመስል የነበረውን ፈጽመው በፅናታቸው ታላቁ የህዳሴ ግድብን በመገንባት ኢትዮጵያን ወደ አዲስ ምዕራፍ አስገብተዋታል” ነው ያሉት።

የዓለም ሃያላን ሀገራት ሃያልነታቸውን ያረጋገጡት በግድብ ነው ያሉት ዶያቆን ዮሴፍ፥ አሜሪካም አሜሪካ የሆነችው “በሁበር ግድብ” ነው ይላሉ።

ቻይና አሁን ለደረሰችበት የእድገት ደረጃ የበቃችው በግድቦቿ መሆኑን በማንሳት ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብም ግዙፍ የልማት መሳሪያ መሆኑን አብራርተዋል።

ኢትዮጵያም በኢኮኖሚ የበለጸጉ ሀገራት የታጠቁትን መሳሪያ በመታጠቋ በተወሰነ ጊዜ ውስጥ መካከለኛ ገቢ ካላቸው ሀገራት ተርታ ትሰለፋለች ነው ያሉት ዲያቆን ዮሴፍ።

ኢትዮጵያውያን ማሳካት የሚፈልጉትን ግብ በማንም ማስፈራሪያ እንደማያቆሙ የተናገሩት አቶ አለባቸው፥ የኢትዮጵያ መንግስትና ህዝብ በግድቡ ግንባታ ያሳዩትም ይህንን ነው ብለዋል።

የግድቡ ሃይል ማመንጨት በኤሌክትሪክ ሃይል እጦት ውስጥ ለሚኖሩ ኢትዮጵያውያን የተስፋ ጎህ ነው ብለዋል።

ኢትዮጵያንም በቴክኖሎጂና በኢንዱስትሪ የበለጸገች ሀገር እንድትሆን የሚያስችል መሆኑንም ጠቅሰዋል።

አቶ ነቢዩ አስፋው በበኩላቸው “ከድሃ እስከ ሀብታም ኢትዮጵያውያን የቻልነውን አዋጥተን የገነባነው እውነተኛ የኢትዮጵያውያንና የአፍሪካውያን ግድብ ሃይል ማመንጨቱ ከእኛ በላይ ዓለምን አስደንቋል” ነው ያሉት።

ኢትዮጵያውያን ከተባበሩ ለምነው ሳይሆን በፈቃዳቸው የራሳቸውን ግብ ማሳካት እንደሚችሉ የግድቡ ስኬት ትልቅ ትምህርት የሰጠ አርዓያ ነው  ብለዋል።

ግድቡ እንዳይገነባ ከተለያዩ አቅጣጫዎች የተከፈቱብንን ጦርነቶች አሸንፈን ሃይል ማመንጨት በመጀመሩ ዳግማዊ አድዋችን ነው ብለዋል።

ኢትዮጵያን እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ‼

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም