በህልውና ዘመቻው የጎላ ሚና ለነበራቸው የፀጥታ ኃይሎች እውቅና ተሰጠ - ኢዜአ አማርኛ
በህልውና ዘመቻው የጎላ ሚና ለነበራቸው የፀጥታ ኃይሎች እውቅና ተሰጠ
ደሴ፤ የካቲት 14/2014 (ኢዜአ) በህልውና ዘመቻው የጎላ አስተዋጽኦ ላበረከቱ የፀጥታ ኃይሎች በደቡብ ወሎ ዞን ኮምቦልቻ ከተማ የምስጋናና እውቅና የመስጠት መርኃ ግብር ተካሄደ።
በመርኃ ግብሩ ላይ የኮምቦልቻ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ ኢንጂነር አህመድ የሱፍ እንዳሉት፤ አሸባሪው ህወሓት ኢትዮጵያን ለማፍረስ በተነሳበት ወቅት በየደረሰበት በህዝብ ላይ ያልፈጸመው ግፍና በደል የለም።
"ይሁን እንጂ ህብረተሰቡ ከሀገር መከላከያ ሠራዊትና ከፀጥታ መዋቅሩ ጋር ተቀናጅቶ ጠላትን በመፋለም ታሪክ የማይሽረው መስዋዕትነት ከፍሏል፣ ድልም አስመዝግቧል" ብለዋል።
እንደ ከንቲባው ገለጻ፤ የእውቅና መርኃ ግብሩ የተዘጋጀው በቀጠናው በተካሄደው የህልውና ዘመቻ የጎላ አስተዋጽኦ ያበረከቱ የመከላከያ ሠራዊት አባላትና ሌሎች የፀጥታ አካላትን ለማመስገን ጭምር ነው።
የምስጋናና የእውቅና መርኃ ግብር መዘጋጀቱ በቀጣይ በጋራ ተንቀሳቅሶ ተጨማሪ ድል ለማስመዝገብ የሚያነሳሳ መሆኑንም ተናግረዋል።
በመርኃ ግብሩ ላይ የመከላከያ ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር አህመዲን መሃመድ፤ በሀገር መከላከያ የደቡብ ዕዝ ዋና አዛዥ ሌተናል ጄነራል ሰለሞን ኢተፋ እንዲሁም የፌደራል፣ የክልልና የዞን አመራሮች፣ የሃይማኖት አባቶች፣ መስዋዕት የሆኑ የፀጥታ ኃይል አባላት ቤተሰቦች እና ሌሎችም የእውቅና ስነስርዓቱ ታዳሚዎች ተገኝተዋል።