ታላቁ የህዳሴ ግድብ ኃይል ማመንጨት የጀመረው ኢትዮጵያ፣ ግብጽና ሱዳን በካርቱም በተፈራረሙት የመርሆች ስምምነት መሰረት ነው - ኢዜአ አማርኛ
ታላቁ የህዳሴ ግድብ ኃይል ማመንጨት የጀመረው ኢትዮጵያ፣ ግብጽና ሱዳን በካርቱም በተፈራረሙት የመርሆች ስምምነት መሰረት ነው
የካቲት 14/2014 (ኢዜአ) የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ኃይል ማመንጨት የጀመረው ኢትዮጵያ፣ ግብጽና ሱዳን በካርቱም በተፈራረሙት የመርሆች ስምምነት መሰረት መሆኑን የውሃ ሃብት አስተዳደር አማካሪ አቶ ፈቅ አህመድ ነጋሽ ገለጹ፡፡
ግድቡ ኃይል ማመንጨት መጀመሩ የታችኛው ተፋሰስ አገራት "የውሃው መጠን ይቀንስብናል" ሲሉ የሚያቀርቡት ስጋት ትክክል አለመሆኑን በተግባር ያሳየ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡
ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ በ13 ተርባይኖች በሙሉ አቅሙ ስራ ሲጀምር አምስት ሺህ 150 ሜጋ ዋት ኃይል ማመንጨት ይችላል፡፡
ከእነዚህ መካከል 375 ሜጋ ዋት ኃይል የሚያመነጨውና "ዪኒት 10" የተባለው ተርባይን በትናትናው ዕለት በጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ ተመርቆ ስራውን አሃዱ ብሎ ጀምሯል፡፡
ሆኖም የታችኛው ተፋሰስ አገራት የሆኑት ግብጽና ሱዳን ግድቡ ኃይል ማመንጨት የጀመረው ሶስቱ አገራት እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር በ2015 በካርቱም የተፈራረሙትን የመርሆች ስምምነት በጣሰ መልኩ ነው የሚል መግለጫ አውጥተዋል፡፡
በሱዳን ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የህዳሴው ግድብ ተወካይ አምባሳደር ኦማር አልፋሩቅ የግብጽ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሳሚ ሽኩሪ ግድቡ ሀይል ማመንጨት መጀመሩ "ሶስቱ አገራት የተናጥል እርምጃ እንዳይወስዱ" በሚል የተፈራረሙትን የመርሆች ስምምነት የሚጥስ ነው የሚል መግለጫ ሰጥተዋል፡፡
ኢዜአ ያነጋገራቸው የውሃ ሃብት አስተዳደር አማካሪ አቶ ፈቅ አህመድ ነጋሽ "ግብጽና ሱዳን ያወጡት መግለጫ የተለመደ የሀሰት ክስ ነው" ሲሉ ተናግረዋል፡፡
ኢትዮጵያ፣ ግብጽና ሱዳን በካርቱም የተፈራረሙት የመርሆች ስምምነት ኢትዮጵያ ከታላቁ የህዳሴ ግድብ ኃይል ማመንጨት የለባትም የሚል አንቀጽ የለውም ብለዋል፡፡
የመርሆች ስምምነት አንቀጽ 5 "ሶስቱ አገራት በውሃ ሙሌትና አለቃቀቅ መመሪያ ላይ ስምምነት ያደርጋሉ፤ የግድቡ ግንባታ በትይዩ ይካሄዳል" የሚል መሆኑን ገልጸዋል፡፡
በመርሆች ስምምነት መመሪያ መሰረ የግድቡ ግንባታ አሁንም 84 በመቶ ስለሆነ ገና ይቀጥላል፤ የግድብ ግንባታ ማለት ደግሞ የውሃ ሙሌትና አለቃቀቅ እንዲሁም ኃይል ማመንጨትንም ይጨምራል ብለዋል፡፡
በመሆኑም ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ውሃ እንዲይዝ የተደረገበት ዋነኛ ዓላማ ኃይል ለማመንጨት ስለሆነ ይህንኑ ስራ ጀምሯል ነው ያሉት፡፡
ከዚህ አኳያ ግድቡ ኃይል ማመንጨት በመጀመሩ የተጣሰ የመርሆች ስምምነትም ሆነ የሚጎዳ ህዝብ የለም ብለዋል፡፡
''ግብፅና ሱዳን የግድቡን ግንባታ እንደማይጎዳቸው ያውቃሉ" የሚሉት አቶ ፈቅ አህመድ፤ በቀጣይ አገራቱ ግድቡን በሚመለከት ለሚከተሉት የተዛባ አካሄድ አስፈላጊውን ምላሽና ትንተና ለመስጠት መዘጋጀት ይገባል ነው ያሉት፡፡
የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ይጠናቀቃል ከተባለበት ከ11አመት በላይ በመጓተቱ በህዝቡ ዘንድ "ግድቡ ያልቃል ወይ" የሚል ጥያቄ አጭሮም እንደነበር አስታውሰዋል፡፡
ለመጓተቱ የገንዘብ እጥረት፣ የውጭ ጫና እና ሌሎች ጉዳዮች ሲጠቀሱ አሁን ላይ ኃይል ማመጨት መጀመሩ ለኢትዮጵያውያን ተስፋና መነሳሳት፣ ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ደግሞ ከድህነት መውጫ መሆኑን ያሳያል ብለዋል፡፡
ግድቡን በፍጥነት አጠናቆ በጨለማ ውስጥ የሚኖረውን ህዝብ የኃይል ተጠቃሚ በማድረግ የዓለም አቀፉ ማህበረሰብ በተሳሳተ መረጃ ኢትዮጵያ ላይ የሚያደርሰውን ጫና መቀነስ ይገባል ነው ያሉት፡፡
ግድቡ ሲሞላም ሆነ ኃይል ማመንጨት ሲጀምር ወደ ታችኛው ተፋሰስ አገራት የሚሄደው ውሃ እንደማይቀንስ በተግባር መታየቱን ጠቅሰው፤ በመሆኑም የታችኞቹ ተፋሰስ አገራት በቅንነት ይህንኑ ሃቅ ሊገነዘቡ እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡