የህዳሴ ግድብ ኃይል ማመንጨት በመጀመሩ መደስታቸውን የጋምቤላ ከተማ ነዋሪዎች ገለጹ - ኢዜአ አማርኛ
የህዳሴ ግድብ ኃይል ማመንጨት በመጀመሩ መደስታቸውን የጋምቤላ ከተማ ነዋሪዎች ገለጹ
ጋምቤላ፤ የካቲት 14/2014 (ኢዜአ) ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ኃይል ማመንጨት በመጀመሩ መደሰታቸውን አስተያየታቸውን ለኢዜአ የገለጹ የጋምቤላ ከተማ ነዋሪዎች ተናገሩ።
የህዳሴ ግድቡ ሙሉ በሙሉ እስኪጠናቀቅ የጀመሩትን ድጋፍ አጠናክረው እንደሚቀጥሉም ነዋሪዎቹ ተናግረዋል።
ከነዋሪዎቹ መካከል አቶ አንዳርጌ ጌታሁን ለኢዜአ በሰጡት አስተያየት እንዳሉት ታላቁ የኢትዮጵያ የህዳሴ ግድብ ኃይል ማመንጨት መጀመሩ የኢትዮጵያውያን የድል አድራጊነት ትንሳኤ ያበሰረ ነው።
በቀጣይም የህዳሴ ግድቡ እስኪ ጠናቀቅ የሚያደርጉትን ድጋፍ አጠናክረው እንደሚቀጥሉም ገልጸዋል።
የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ኃይል ለማመንጨት በመብቃቱ ደስታ እንደተሰማቸው የገለጹት ደግሞ ሌላው የከተማዋ ነዋሪ አቶ ሳሙኤል ኡቡያ ናቸው።
የግድቡን ቀሪ ስራዎች ለማጠናቀቅም ሁሉም ኢትዮጵያውያን እንደ ካሁን በፊቱ በጋራ መረባረብ እንዳለባቸውም ተናግረዋል።
አቶ አንዳርጌ ዋሲሁን በበኩላቸው ኢትዮጵያ ባለፉት ሶስት ዓመታት የተለያዩ ፈተናዎችን በመቋቋም የታላቁ የህዳሴ ግድብ ኃይል ለማመንጨት መብቃቱ የኢትዮጵያውያንን ድልና ደስታ እጥፍ ያደርገዋል ብለዋል።
የህዳሴ ግድቡ የሁሉም ኢትዮጵያውያን አሻራ ያረፈበት ፕሮጀክት እንደመሆኑ በቀጣይም ህዝቡ የፕሮጀክቱን ቀሪ ስራ ለማጠናቀቅ የተጀመረውን ተሳትፎ አጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ ህዝቦች የአንድነት መገለጫ አርማ የሆነው የህዳሴ ግድብ ኃይል ማመንጨት በመጀመሩ ለመላው የኢትዮጵያ ህዝብ እንኳን ደስ አላቹህ በማለት ሀሳባቸውን የጀመሩት ደግሞ አቶ ኡቦንግ ኡጃቶ ናቸው።
ታላቁ የህዳሴ ግድብ ሃይል ማመንጨት መጀመሩ ከድህነትና ከስንዴ ልመና የምንወጣበት ጊዜ ሩቅ አለመሆኑን የሚያመለክት ነው ብለዋል።
''የህዳሴ ግድብ ከዚህ ደረጃ ለመድረሱ ዋነኛው ሚስጥር የኢትዮጵያ ህዝቦች በአንድነት መቆም ነው'' ያሉት አቶ ኡቦንግ ግድቡ እስኪጠናቀቅ ህብረተሰቡ ድጋፉን አጠናክሮ ማስቀጠል እንደሚገባው ገልጸዋል።
የህዳሴ ግድብ አንደኛው ዩኒት ትናንት በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ተመርቆ በይፋ ስራ መጀመሩ የሚታወቅ ነው።