ቀጥታ፡

ህዳሴ ሃይል ማመንጨት መጀመሩ ኢትዮጵያ የተፈጥሮ ሀብቷን አልምታ መጠቀም እንደምትችል ማሳያ ነው

ፍቼ/  የሆሳዕና /የአሶሳ/ሶዶ የካቲት 13/2ዐ14/ኢዜአ/ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የኤሌትሪክ ሃይል ማመንጨት መጀመሩ ኢትዮጵያ የተፈጥሮ ሀብቷን አልምታ መጠቀም እንደምትችል ማሳያ ነው ሲሉ የተለያዩ ከተማ ነዋሪዎች ገለጹ፡፡

የፍቼ ከተማ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ታላቁ የህዳሴ ግድብ  ዛሬ የኤሌትሪክ ኃይል ማመንጨት በመጀመሩ  የተሰማቸውን ደስታ ገልጸዋል።

አስተያየታቸውን ለኢዜአ ከሰጡት ነዋሪዎች መካከል ሀገራችን በተፈጥሮ ሀብቷ ያለምንም ከልካይ ከመጠቀም ባሻገር የጋራ ተጠቃሚነት ላይ ያላትን ፅኑ አቋም እንደሚያመለክትም ጠቁመዋል፡፡

ግድቡ ለፍፃሜ እስኪበቃ ቦንድ በመግዛት ችግኞችን በመትከልና በአካባቢያቸው ያሉ ተፋሰሶችን ከደለል በመጠበቅ አስፈላጊውን ስራ እንደሚሰሩም አረጋግጠዋል።

የኢትዮጵያ ሕዝብና መንግሥት ግድቡን ገንብቶ የውሃ ሙሌቱን በብርቱ ትግል በከፊል በማከናወን ለኤሌትሪክ ኃይል ማመንጨት መብቃቱ እጅግ የሚያስደስትና የሀገሪቱን ሕዝቦች የሚያኮራ ተግባር እንደሆነም ገልጸዋል፡፡

 የሆሳዕና ከተማ ነዋሪዎች በበኩላቸው ኢትዮጵያውያን አንድነታችንን ካጠናከርን የነገ ክፍታችን የተሻለ ማድረግ የምንችል መሆናችንን ያረጋገጥንበት ዕለት ነውም ብለዋል።

ዕድግትና ብልፅግናዋን ለማይፈልጉ የግድቡን ግንባታ እንደ ተግዳሮት በመውሰድ ለማስተጓጎል ሲጥሩ የነበሩ የውስጥና የውጭ ኃይሎችን አንገት ያስደፋንበት ቀን መሆኑንም ተናግረዋል።

የአሶሳ ነዋሪች ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ተጠናቆ በሙሉ አቅሙ ኃይል እስከሚያመነጭ ድረስ እያደረጉት ያለውን ሁሉ አቀፍ ድጋፍ አጠናክረው እንደሚቀጥሉ አስታወቁ፡፡


''ሀገር ህዝብን በሚያዳምጥ መንግሥት ስትመራ የሚከናወኑ ፕሮጀክቶች ውጤታማ ይሆናሉ'' ያሉት ነዋሪው የህዳሴው ግድብ ፈተናዎችን አልፎ ኃይል ለማመንጨት መብቃቱ ለዚሁ ማሳያ ነው  ብለዋል፡፡

 የሶዶ ከተማ ነዋሪችም  ግድቡ በተለያዩ ምክንያቶች ሊጓተትና በተቀመጠለት ጊዜ ሳይጠናቀቅ በመዘግየቱ ቅሬታ አሳድሮባቸው እንደነበር ገልጸዋል።

ለውጡን ተከትሎ የተወሰደው ቆራጥ እርምጃ ታዲያ ከፕሮጀክቱ ጋር ተያይዘው የነበሩ ችግሮችን በማረም  ስራው በጥራትና በፍጥነት እንዲከናወን አድርጎታል ብለዋል።

ግድቡ ከልጅ እስከ አዋቂ የሁሉም አሻራ ያረፈበት ነው ያሉት አስተያየት ሰጪው ይህም የጋራ ጥረት ውጤታቸውን በመሆኑ በስኬቱ መደሰታቸውን ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም