ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ኃይል ማመንጨት መጀመሩ በራሳችን አቅም ግዙፍ የልማት ስራዎችን እውን ማድረግ እንደምንችል አመላካች ነው - ኢዜአ አማርኛ
ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ኃይል ማመንጨት መጀመሩ በራሳችን አቅም ግዙፍ የልማት ስራዎችን እውን ማድረግ እንደምንችል አመላካች ነው
የካቲት 13/2014 (ኢዜአ) ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ኃይል ማመንጨት መጀመሩ በራሳችን አቅም ግዙፍ የልማት ስራዎችን እውን ማድረግ እንደምንችል አመላካች ነው ሲሉ ኢዜአ ያነጋገራቸው የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዎች ገለፁ።
ነዋሪዎቹ ግድቡ ሙሉ ለሙሉ እስኪጠናቀቅ ድረስ የሚያደርጉትን ድጋፍ አጠናክረው እንደሚቀጥሉም ቃል ገብተዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ ታላቁ የህዳሴ ግድብን ኃይል የማመንጨት ስራ በዛሬው እለት በይፋ አስጀምረዋል፡፡
በዚህም ግድቡ ካሉት 13 ተርባይኖች መካከል 'ዩኒት 10' የተሰኘው ተርባይን 375 ሜጋ ዋት ኃይል የማመንጨት ስራውን በዛሬው እለት ጀምሯል፡፡
የግድቡን ኃይል ማመንጨት አስመልክቶ ኢዜአ ያነጋገራቸው የአዲስ አበባ ነዋሪዎችም እለቱ ለኢትዮጵያዊያን ልዩ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
የመዲናዋ ነዋሪ የሆኑት አቶ መብራቱ ጌታቸው ግድቡ ኃይል ማመንጨት መጀመሩ የኢትዮጵያን ከድህነት የመውጣት ጉዞ ጅምር አብሳሪ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ግድቡ የአሁኑ ትውልድ የራሱን አኩሪ ታሪክ ለመጪው ትውልድ የሚያስቀምጥበት መሆኑንም ነው የተናገሩት፡፡
ሌላው አስተያየት ሰጪ አማኑኤል ታምሩ በበኩላቸው ለግድቡ ግንባታ በተለያየ ጊዜ ቦንድ በመግዛት ድጋፍ ማድረጋቸውን ገልፀው፤ ግድቡ እስኪጠናቀቅ ድጋፋቸውን አጠናክረው እንደሚቀጥሉም ተናግረዋል።
ግድቡ ኃይል ማመንጨት መጀመሩ ኢትዮጵያዊያን የትኛውንም ፈተና ተቋቁመው ግዙፍ የልማት ስራዎችን እውን እንደሚያደርጉ ማሳያ መሆኑን የተናገሩት ደግሞ አቶ ሀሰን አህመድ ናቸው።
ዲያቆን አምላኩ ወዳጄ በበኩላቸው የህዳሴ ግድብ የኢትዮጵያ የእድገት ተስፋ መሆኑን ጠቅሰው፤ የግድቡ በአድዋ ድል መታሰቢያ ሰሞን ኃይል ማመንጨት መጀመሩ ለኢትዮጵያዊያን ድርብ ድል መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ታላቁ የህዳሴ ግድብ እንደ አድዋ ድል ሁሉ የኢትዮጵያዊያን የአንድነትና የመተባበር ምልክት መሆኑንም ነው ያስረዱት፡፡