የህዳሴ ግድብ ኃይል ማመንጨት በመጀመሩ የተለያዩ ከተማ ነዋሪዎች ደስታቸው በመግለፅ ላይ ናቸው - ኢዜአ አማርኛ
የህዳሴ ግድብ ኃይል ማመንጨት በመጀመሩ የተለያዩ ከተማ ነዋሪዎች ደስታቸው በመግለፅ ላይ ናቸው
ሚዛን፣ የካቲት 13/2014 (ኢዜአ) ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ዛሬ ኃይል ማመንጨት መጀመሩ የአሸናፊነታችን አርማና የአንድነታችን ውጤት በመሆኑ ኩራትና ደስታ እንደተሰማቸው የሚዛን አማንና የባቲ ከተማ ነዋሪዎች ገልፀዋል፡፡
ነዋሪዎቹ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ውስብስብ ችግሮችን አልፎ ኃይል ማመንጨት መጀመሩ ኢትዮጵያውያን በአንድነት የማንሻገረው ችግር እንደሌለ ተጨባጭ ማሳያ ነው ብለዋል፡፡
የሚዛን ነዋሪ የሆኑት አቶ ታምሩ ዳብን ለኢዜአ በሰጡት አስተያየት ግድቡ ኃይል አመንጭቶ በማየታቸው የተሰማቸውን ደስታ ገልጸው ይህም "የእኛ ኢትዮጵያዊያን የአሸናፊነት ማረጋገጫችን ነው" ብለዋል።
ሕፃን አዋቂ ሳይል ሁሉም ያለውን አዋጥቶ ያስገነባው ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ለእዚህ ደረጃ መብቃቱ የሚያኮራ ተግባር መሆኑንም ገልጸዋል።
ወይዘሮ በረከት ተካልኝ በበኩላቸው ግድቡ የመጀመሪያ ምዕራፍ ኃይል ማመንጨት መጀመሩን ሲሰሙ ጥልቅ ደስታ እንደተሰማቸው ገልጸዋል።
"እኛ ኢትዮጵያውያን በራሳችን ማንኛውንም ልማት እውን ማድረግ እንደምንችል ከአድዋ ድል ቀጥሎ ታላቁ ህዳሴ ግድብ ህያው ምስክራችን በመሆኑ ኮርቻለሁ" ብለዋል።
ህዳሴ ግድቡ የሁላችንንም አሻራ ያረፈበት፣ ከጨለማ የሚያወጣን የጋራ ብሄራዊ ሀብታችን ነው ያሉት ደሞ የባቲ ከተማ ነዋሪ ሼህ ሁሴን ሰይድ ናቸው።
የግድቡ ኃይል ከመስጠቱና የዘመናት ችግራችን መፍታት ከመጀመሩም በላይ አንድነታችን ለማጠናከር፣ ብሄራዊ መግባባት ለመፍጠርና በጋራ ማልማት እንደምንችልም አስተምሮናል ብለዋል።
ወጣት ፎዚያ ከበደ በበኩሏ የህዳሴ ግድቡ ውሳዊና ውጫዊ ጫናዎችን በብርቱ ተቋቁሞ ኃይል ማመንጨት መጀመሩ ሀገራዊ ዲፕሎማሲውን ለማጠናከር፣ የውጭ ጫናውን ለማቃለልና አንድነታችንን ለማጠናክር ያግዛል ብላለች።
የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ በተለይም ለወጣቱ ዘርፈ ብዙ ተስፋዎችን የሰነቀና የቀጣይ የኢኮኖሚ መሰረታችን በመሆኑ ለፍሬ መብቃቱ ድርብ ደስታ መሆኑን ገልጻለች።
የዛሬው የግድቡን ግንባታ ለማስተጓጎል ተባብረው ይሰሩ የነበሩ አንዳንድ የውጥና የውጭ ኃሎችን ያሳፈረ፤ ወዳጆቻችንን ደግሞ ደስታ ያጎናፀፈ ልዩ ቀን ነው ስትልም ተናግራለች።
የግድቡ ቀሪ የኃይል ማመንጫ ስራዎች ተጠናቀው ሙሉ በሙሉ አገልግሎት እንዲሰጡ እያደረጉት ያለውን ድጋፍ በበለጠ አጠናክረው እንደሚቀጥሉ አስተያየት ሰጪዎቹ አረጋግጠዋል።
የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የሃይል ማመንጨት ማብሰሪያ ስነ-ስርአት ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ጨምሮ ሌሎች ከፍተኛ የመንግስት የስራ ሃላፊዎች በተገኙበት ዛሬ መከናወኑ ይታወሳል፡፡