ቀጥታ፡

ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ በመላው የሀገራችን ህዝቦች ላብ የተገነባ የአፍሪካ የብርሀን ማማ ነው

የካቲት 13 ቀን 2014 (ኢዜአ) ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ በመላው የሀገራችን ህዝቦች ላብ የተገነባ የአፍሪካ የብርሀን ማማ ነው ሲሉ የደቡብ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ እርስቱ ይርዳ ገለጹ።

ግድቡ ሀይል ማመንጨት መጀመሩን በማስመልከት ለመላው ኢትዮጵያውያንና የክልሉ ህዝብ የ’እንኳን ደስ ያላችሁ’ መልዕክት አስተላልፈዋል።

አቶ እርስቱ በመልዕክታቸውም ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ በኢትዮጵያውያን ላብ የተገነባ የአፍሪካ የብርሀን ማማ መሆኑን ገልጸዋል።

የክልሉ ህዝብ ሳይተርፈው ከመቀነቱ እየፈታ ፕሮጀክቱ እውን እንዲሆን ላደረገው የላቀ አስተዋጽኦ በራሳቸው እና በክልሉ መንግስት ስም ምስጋና ያቀረቡት ርዕሰ መስተዳድሩ፤ “አንድነታችንን ካጠናከርን እና ከተባበርን ድህነት ታሪክ ይሆናል” ብለዋል።

“የኢትዮጵያ ክብር እና ዝናዋ ከዚህም በላይ ደምቆ እንደሚታይ እምነቴ የጸና ነው” ያሉት አቶ እርስቱ፤ “ጠላቶቻችን ጠፉ ከሰሙ ሲሉን በከፍታ ላይ እንገኛለን” ብለዋል።

የህዳሴ ግድቡ ሃይል ማመንጨት መጀመር የተጀመረው የብልጽግና ጉዞ አንዱ ማሳያ መሆኑን ገልጸው፤ ከውስጥም ሆነ ከውጭ ኢትዮጵያን ለማፈራረስ እና ለመበተን የተዘረጋውን ደባ በማክሸፍ በጠነከረ ክንዳችን ጨለማውን ገፈን ብርሐን ማየት ችለናል ሲሉ ገልጸዋል።

በብርሐን ውስጥ ጉልበት፣ አንድነት፣ እድገት እና ብልጽግና ጎልቶ ይታያል ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ ጥንት ጀግኖች አባቶቻችን በክብር ያቆዩልንን ገናና ሀገር በጽኑ መሰረት ላይ በመገንባት ትንሳኤዋን እናያለን ብለዋል።

ርዕሰ መስተዳድሩ የፕሮጀክቱ የመሠረት ድንጋይ ከተቀመጠ ጀምሮ የአካባቢው ሙቀት ሳይበግራቸው ሌት ተቀን ሲደክሙ ለነበሩ ሁሉ እንኳን የጥረታችሁን ውጤት ለማየት በቃችሁ ሲሉም ተናግረዋል።

በጊዜ ሳይወሰኑ ፕሮጀክቱን በንስር እይታ በመከታተል ሙያዊ ሀላፊነታቸውን እየተወጡ ላሉ ጀግኖቻችንም አድናቆታቸውን ገልጸዋል።

ርዕሰ መስተዳድሩ በመልዕክታቸው እንዳሉት ይህንን የድል ብርሐን ማየት በመቻላችን ለመላው ለሀገራችን እና ለክልላችን ህዝቦች እንኳን ደስ ያላችሁ !! ለማለት እወዳለሁ ብለዋል።

ኢትዮጵያን እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ‼

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም