ቀጥታ፡

"የማይዝሉ የተባበሩ ክንዶቻችን ዓባይን ወደ ብርሃን ቀይረዋል"-የሲዳማ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ደስታ ሌዳሞ

ሀዋሳ የካቲት 13/2014 (ኢዜአ) "የማይዝሉ የተባበሩ ክንዶቻችን በጉባ ላይ ታሪክ በመስራት ዓባይን ወደ ብርሃን መቀየር ችለዋል" ሲሉ የሲዳማ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ርዕሰ መስተዳድር አቶ ደስታ ሌዳሞ ገለጹ።
ርዕሰ መስተዳድር ደስታ የታላቁ የኢትዮጵያ  ሕዳሴ ግድብ  የኤሌክትሪክ  ኃይል  ማመንጨት ብስራትን አስመልክተው ለመላው ኢትዮጵያውያን እንኳን ደስ አላችሁ መልዕክት አስተላልፏል።

ኢትዮጵያውያን ለዘመናት በብዕሮቻችን፣ በግጥሞቻችን፣ በዜማዎቻችን  ስለዓባይ  ወንዝ ቁጭታችንን፣ መሻታችንን  እና ፍቅራችንን   ስንገልፅ  መቆየታችንን  አስታውሰዋል ።

ዛሬ ይህ ሁሉ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ መቀየሩን ርዕሰ መስተዳድሩ ጠቅሰው፤ "የህዳሴው  ግድብም የአንድነት ማስተሳሰሪያ ገመዳችን ነው" ብለውታል።

እንዲሁም የአይበገሬነት ምልክታችን እና የሕብረ ብሔራዊ አርማችን መሆኑን ነው ያመለከቱት ርዕሰ መስተዳድሩ በመልዕክታቸው።

ከዚህም ባለፈ የጋራ ታሪክ  አሻራችንና ማህተማችን መሆኑን ገልጸው፤ ይህም ለመጪው ትውልድ የታሪክ ሐውልት ሆኖ የሚተላለፍ ቅርስ  ነው ብለዋል።

ለዘመናት ዓባይ ከኢትዮጽያ እምብርት ፈልቆ የባዕድ ሀገር ሲሳይ ሲሆን ማየቱ ሲቆጨንና ሲያብከነክነን ቢቆይም የኋላ-የኋላ የዓባይን  ቱሩፋትና  በረከት  ተቋዳሽ  በመሆናችን  ኢትዮጵያውያን እንኳን ደስ አላችሁ ብለዋል።

ግድቡ መጋቢት 24 ቀን 2003 ዓ.ም በቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል በጉባ የመሰረተ ድንጋይ ሲቀመጥ መላ ኢትዮጵያውያን ከዳር እስከዳር ተንቀሳቅሰው በገንዘባቸው፤ በዕውቀታቸው በላባቸው እንደሚገነቡት የገቡትን ቃል ተግበራዊ መጀመሩን አስታውሰዋል።

ይሁንና ይህ የመላው ኢትዮጵያውያን አይንና አሻራ ያረፈበት ግድብ በታቀደለት ጊዜ እንዳይጠናቀቅ "ከውስጥም ሆነ ከውጭ ከባድ ፈተናዎችና ተግዳሮቶች ገጥመውን እንደነበረ ሁላችንም የምንረዳው ሀቅ ነው" ብለዋል።

መንግሥት ከሀገራዊ ለውጡ ማግስት ጀምሮ ለፕሮጀክቱ ልዩ ትኩረት  በመስጠት  ከላይ እስከታች የአመራርና  የአሰራር  ለውጥ በማድረግ ፤ ህዝቡን  ዳግም  በማነቃቃትና በማስተባበር የላቀ ሚና መጫወቱን ተናግረዋል።

በተለይ ፕሮጀክቱ በታቀደለት ጊዜ እንዳይጠናቀቅ ተግዳሮት የሆኑ ብልሹ አሰራሮችን በማቃናት፤ ግድቡ እውን እንዳይሆን የሚፈልጉ የውጭ ጠላቶቻችንን ጫና ተቋቁሞ፤ ድብቅና ስውር ሴራዎችን አምክኖ፤ ግድቡ ለህዝባችን ጥቅም ላይ እንዲውል እልህ አስጨራሽ ትግል አድርጎ አሁን ለመጣው ፍሬ አብቅቶታል ሲሉ አድንቀዋል።

እኛ ኢትዮጵያዊያን ለህዳሴው ግድብ ያደረግነው ህብረት፤አንድነትና ጥንካሬ፤የአልበገሬነትና የዓላማ ፅናታችንን ያሳየ ነው ብለዋል ርዕሰ መስተዳድር ደስታ።

የአባይን ግድብ እውን ማድረግ ብቻ ሳይሆን ቀጣይ ዓላማ ሰንቀን ለተነሳንበት ብልፅግና ጉዞ ብሩህነት ማሳያ መሆኑንም አስምረውበታል።

ርዕሰ መስተዳድር ደስታ ባስተላለፉት የደስታ በመልዕክታቸው በዚህም  የኢትዮጵያ  ትንሳኤና የብልፅግና ግባችን እሩቅ እንደማይሆን ማረጋገጥ ይቻላል ብለዋል።

እኛ ኢትዮጵውያን አንድነታችን አጠናከረን በጋራ ከተጓዝን ማንም ከውጥናችን ሊያግደን እንደማይችል አውስተዋል።

ይህ ትውልድ የታላቁ ኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ህያው  ምስክር መሆን  መቻሉን  አመላክተው ይህ አንድነታችንንና የመንፈስ ጥንካሬያችንን በልማትና በብልፅግና ጉዞ መድገም ይኖርብናል ሲሉም አስገንዝበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም