ቀጥታ፡

የታላቁ የህዳሴ ግድብ ኃይል ማመንጨት መጀመር ትውልዱ ህልሙን እውን ማድረግ እንደሚችል ያመላከተ ነው

አዲስ አበባ የካቲት 13/2014 (ኢዜአ) "የታላቁ የህዳሴ ግድብ ኃይል ማመንጨት መጀመር የአሁኑ ትውልድ ህልሙን እውን ማድረግ እንደሚችል ያመላከተ ነው" ሲሉ የመከላካያ ሚኒስትርና የግድቡ ስራ አመራር ቦርድ ሰብሳቢ ዶክተር አብርሃም በላይ ተናገሩ፡፡
ሚኒስትሩ በታላቁ የህዳሴ ግድብ የኃይል ማመንጨት ማብሰሪያ መርሃ-ግብር ላይ ተገኝተው ባስተላለፉት መልዕክት ግድቡ በርካታ ውጣ ውረዶችን አልፎ ለፍሬ በቅቷል ብለዋል፡፡

ግድቡ ከጥንስሱ እስከ ዛሬ በአመራር ቅብብሎሽ እና በፍትሃዊ የውሃ ተጠቃሚነት ትግል ለስኬት መብቃቱንም ነው ያብራሩት፡፡

የግድቡ ግንባታ በምህንድስናው ዘርፍ ውስብስብ ስራዎች የተከናወኑበት መሆኑን ጠቅሰው፤ ይህም ኢትዮጵያ በመስኩ ያላትን ልምድ ከፍ ወዳለ ደረጃ እንዲሸጋገር አድርጓል ነው ያሉት፡፡

ባለፉት አራት ዓመታት ፕሮጀክቱ ላይ ተከስተው የነበሩ ጉልህ ችግሮችን ለመፍታት የተተገበሩ ሳይንሳዊ መፍትሄዎች ለውጤታማነቱ መሰረት መሆናቸውንም ገልጸዋል፡፡

ለግድቡ ግንባታ ስኬት አስተዋጽኦ ላበረከቱ አካላትም ምስጋና አቅርበዋል፡፡

የግድቡ ኃይል ማመንጨት መጀመር በአገሪቱ በየዓመቱ በ13 በመቶ እያደገ የመጣውን የኃይል አቅርቦት ፍላጎት በመመለስ የህዝቡን ኑሮ ለማሻሻል ሚናው የጎላ መሆኑንም አብራርተዋል፡፡

ፕሮጀክቱ ለአካባቢ ጥበቃ፣ ለቱሪዝምና ሌሎች ተያያዥ የልማት ስራዎች መነሻ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡

በቀጣይ የግድቡን ቀሪ ስራዎች በስኬት ለማጠናቀቅ በትኩረት እንደሚሰራም ነው የተናገሩት፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም