ቀጥታ፡

"በአንድ ልብ ና በአንድ ሃሳብ የምንቆምበት ጊዜው አሁን ነው"

አዲስ አበባ የካቲት 13/2014 (ኢዜአ)"በአንድ ልብና በአንድ ሃሳብ የምንቆምበት ጊዜው አሁን ነው" ሲሉ የቀድሞው የኢፌዲሪ ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ኃይለማሪያም ደሳለኝ ተናገሩ፡፡
አቶ ኃይለማርያም ይህን ያሉት በታላቁ ህዳሴ ግድብ ኃይል ማመንጨት ማብሰሪያ መርሃ-ግብር  ላይ ተገኝተው ባደረጉት ንግግር ነው፡፡

አፍሪካ በርካታ ሃብት ቢኖራትም ለበርካታ ዓመታት በተሰራባት የከፋፍለህ ግዛ ፖሊሲ ምክንያት ሃብቶቿን መጠቀም ሳትችል መቆየቷን አስታውሰዋል፡፡

ከዚህ አኳያ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ አፍሪካ ያሏትን ጸጋዎች በራሷ አቅም መጠቀም እንድትችል ተምሳሌት የሚሆን ፕሮጀክት መሆኑንም አንስተዋል፡፡

እኛ ኢትዮጵያዊያን ያሉን የሃሳብ ልዩነቶች ሳያባሉን ለመጪው ትውልድ የተሻለ አገርን ለማስረከብ መስራት አለብን ሲሉም ነው የተናገሩት፡፡

የጦረኝነት ስነ-ልቦና ልማትን በመግታት በድህነት ለመማቀቅ ምክንያት እንደሚሆን የገለጹት አቶ ኃይለማርያም፤ ከውጊያ ይልቅ ልማትን፤ ከመከፋፋል ይልቅ አንድነትን ማስቀደም ይገባል ብለዋል፡፡

ከዚህ አኳያ "በአንድ ልብ በአንድ ሃሳብ የምንቆምበት ጊዜው አሁን ነው" ሲሉም ነው የተናገሩት፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም