ኢትዮጵያ ማንንም የመጉዳት ፍላጎት የላትም፤ ፍላጎቷም ኤሌክትሪክ አይተው የማያውቁ ዜጎቿን የኃይል ተጠቃሚ ማድረግ ነው - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ ማንንም የመጉዳት ፍላጎት የላትም፤ ፍላጎቷም ኤሌክትሪክ አይተው የማያውቁ ዜጎቿን የኃይል ተጠቃሚ ማድረግ ነው
አዲስ አበባ የካቲት 13/2014 (ኢዜአ)"ኢትዮጵያ ማንንም የመጉዳት ፍላጎት የላትም፤ ፍላጎቷም ኤሌክትሪክ አይተው የማያውቁ ዜጎቿን የኃይል ተጠቃሚ ማድረግ ነው" ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ ተናገሩ፡፡
ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ በበርካታ ፈተናዎች ውስጥ አልፎ ኃይል የማመንጨት ሥራውን ዛሬ በይፋ ጀምሯል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ የግድቡን ኃይል የማመንጨት ስራ ባስጀመሩበት ወቅት ባስተላለፉት መልዕክት "ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የአንድነታችን፣ የመነሳታችን፣ የማደጋችን እና የአይበገሬነታችን ምልክት ነው" ብለዋል።
"ኢትዮጵያ ማንንም የመጉዳት ፍላጎት የላትም፤ ፍላጎቷም ኤሌክትሪክ አይተው የማያውቁ ዜጎቿን የኃይል ተጠቃሚ ማድረግ ነው" ሲሉም ተናግረዋል።
ግድቡ ለኢትዮጵያ እና ኢትዮጵያውያን ከጨለማ እና ከድህነት መውጫ ድልድይ ሆኖ በማገልገል ረገድ ትልቅ ተስፋን የሚሰጥ እንደሆነም ገልጸዋል።
ግድቡ ኃይል የማመንጨት ስራውን መጀመር ለኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ለታችኛው ተፋሰስ አገራትም ጭምር ታላቅ የምሥራች ነው ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትሩ፡፡
ግድቡ የሚያመነጨውን ኃይል ከጎረቤት አገራት ባለፈ አፍሪካን ለማስተሳሰር ጉልህ ሚና እንዳለው አስረድተዋል፡፡
ኢትዮጵያ ከፍተኛ የውሃ ሃብት ያላት አገር እንደመሆኗ መጠን በርካታ ግድቦችን በመገንባት ሃይል የማምረት እና የመሸጥ እምቅ አቅም አላት ነው ያሉት።
በመሆኑም የበለጸጉ አገራት አሁን ያለውን የውሃ ፖለቲካ መልክ በመቀየር በመስኩ ከኢትዮጵያ ጋር በትብብር መስራት እንዳለባቸው ጠቅሰው፤ በዚህም በርካታ አገራትን ተጠቃሚ ማድረግ ይቻላል ብለዋል፡፡
የግድቡ ግንባታ በኢትዮጵያዊያን ቅብብሎሽ እውን መሆኑን ያነሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ የግድቡን ጽንሰ-ሃሳብ ከማስጀመር አንስቶ እዚህ እንዲደርስ ላደረጉ የቀድሞ የኢትዮጵያ መሪዎች፣ ሚኒስትሮች፣ ባለሙያዎችና ሰራተኞች ምስጋና አቅርበዋል፡፡
በተጨማሪ የዳያስፖራ እና ዲፕሎማቲክ ማህበረሰብ አባላት እንዲሁም መላ ኢትዮጵያዊያን ለግድቡ ግንባታ ገንዘብ ከማዋጣት ባሻገር አስፈላጊ በሆነበት ቦታ ሁሉ ድምጻቸውን በማሰማት ላበረከቱት አስተዋጽኦም ምስጋና አቅርበዋል።