ቀጥታ፡

ዓባይ የቁጭት ዘፈን መነሻ ከመሆን አልፎ የሀገር ኢኮኖሚንና የህብረተሰቡን ኑሮ ለመለወጥ በቅቷል

አዲስ አበባ የካቲት 13/2014 (ኢዜአ) ዓባይ የቁጭት ዘፈን መነሻ ከመሆን አልፎ የሀገር ኢኮኖሚንና የህብረተሰቡን ኑሮ ለመለወጥ በቅቷል ሲሉ የታላቁ ህዳሴ ግድብ ፕሮጀክት ስራ አስኪያጅ ኢንጂነር ክፍሌ ሆሮ ተናገሩ፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ የታላቁ የህዳሴ ግድብን  የኃይል ማመንጨት ስራ ዛሬ በይፋ አስጀምረዋል፡፡

በ13 ተርባይኖች አምስት ሺህ 150 ሜጋ ዋት የሚያመነጨው ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ 357 ሜጋ ዋት ስራውን አሃዱ ብሎ ዛሬ ጀምሯል፡፡

የግድቡ ስራ አስኪያጅ ኢንጂነር ክፍሌ ሆሮ በዚህ ወቅት የግድቡ ግንባታ የኤሌክትሮ ሜካኒካል ስራ ሲያከናውን ከነበረው የብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን ጋር በተያያዘ መዘግየት አጋጥሞት እንደነበር አስታውሰዋል፡፡

ከለውጡ ማግስት ወደ ኃላፊነት የመጣው አመራር በሰጠው አፋጣኝ ውሳኔ ችግሩን መቅረፍ መቻሉን ተናግረዋል፡፡

ኢትዮጵያዊያን እና መንግስት ያለምንም የውጭ እርዳታ ለግድቡ ግንባታ ከአንድ ነጥብ 65 ቢሊዮን ብር በላይ ድጋፍ ማድረጋቸውንም ገልጸዋል፡፡

በአሁኑ ወቅት የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ የፕሮጀክት አፈፃፀም 84 በመቶ መድረሱን ጠቅሰው፤ ኮቪድ 19 ወረርሽኝና የግድቡን ግንባታ ለማስተጓጎል የተከፈቱ የተልዕኮ ጦርነቶች የግንባታ ሂደቱን ፈትነውታል ብለዋል፡፡

ይሁን እንጂ ኢትዮጵያውያን የገጠሟቸውን ፈተናዎች በጋራ በመቋቋም ትልቅ ነገር ማከናወን እንደሚችሉ አሳይተዋል ነው ያሉት፡፡

በዚህም ዓባይ የቁጭት ዘፈን መነሻ ከመሆን አልፎ የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ እና የህብረተሰቡን የኑሮ ደረጃ በማሳደግ አወንታዊ አስተዋጽኦ ማድረግ የሚችልበት ደረጃ ላይ ደርሷል ብለዋል፡፡

እኛ የዚህ ዘመን ትውልዶች የአባቶቻችንን ህልም እውን በማድረግ ውድቀታችንን ለማየት የሚቋምጡ ኃይሎችን ምኞት ባዶ አስቀርተናል ብለዋል፡፡

ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ በዓመት 15 ሺህ 760 ጊጋ ዋት ኃይል ከማመንጨትም ባሻገር ለአሳ እርባታ እና ቱሪዝም ምቹ ሁኔታ የሚፈጥር መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ግድቡ የሚይዘው ውሃ ወደ ኋላ 240 ኪሎ ሜትር የሚዘረጋ ሲሆን፤ ይህም  የጣና ሀይቅ ከሚይዘው ውሃ ሁለት ነጥብ አምስት እጥፍ የሚልቅ በኢትዮጵያ በትልቅነቱ የመጀመሪያ የሆነ ሰው ሰራሽ ሀይቅ ይፈጥራል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም