ሳዑዲ ዓረቢያ ኢትዮጵያውን እስረኞችን ልትፈታ ነው - ኢዜአ አማርኛ
ሳዑዲ ዓረቢያ ኢትዮጵያውን እስረኞችን ልትፈታ ነው
አዲስ አበባ ግንቦት 10/2010 የሳዑዲ ዓረቢያ መንግስት ኢትዮጵያውያን እስረኞችን ለመፍታት ዝግጁ መሆኑን ገለጸ። ኢዜአ ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ባገኘው መረጃ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ (ዶክተር) ከሳዑዲ ዓረቢያ አልጋ ወራሽ መሀመድ ቢን ሰልማን ጋር ተወያይተዋል። በውይይቱ ወቅት ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ በተለያዩ ምክንያቶች በሳዑዲ ዓረቢያ በህግ ጥላ ስር የሚገኙ ኢትዮጵያውያን እንዲፈቱ ጥያቄ አቅርበዋል። ሳዑዲ አረቢያም ጥያቄውን በመቀበል ኢትዮጵያውያን ዜጎችን እንደምትፈታ አስታውቃለች። የሳዑዲ ዓረቢያ አልጋ ወራሽ መሀመድ ቢን ሰልማን በውይይቱ ወቅት እንደገለጹት፤ ኢትዮጵያ የምታደርገውን የልማት ጥረት ሳዑዲ አረቢያ ትደግፋለች። በውይይቱ ሁለቱ አገሮች ትርጉም ያለው የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት ለማድረግ፣ በኢነርጂ እና ግብርና ዘርፍ ያለውን ትብብር ለማጠናከር ተስማምተዋል። አገሮቹ ኢትዮጵያ ያላትን የቱሪዝም ሀብት ለመጠቀም እና ለማጎልበት በትብብር ለመስራትም ተስማምተዋል። ሳዑዲ ዓረቢያ እና ኢትዮጵያ የኤሌትሪክ ኃይል መስመሮችን ማገናኘት በሚቻልበት ዙሪያ ጥናት ለማድረግ ስምምነት ላይ መድረሳቸው ታውቋል። የሳዑዲ ዓረቢያ ባለሀብቶች በኢትዮጵያ ኢንቨስት እንዲያደርጉ እንደሚያበረታቱም አልጋ ወራሽ መሀመድ ቢን ሰልማን ገልጸዋል። ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ የሳዑዲው ነንጉስ ቢን ሰልማን አብዱልአዚዝ ባደረጉላቸው ግብዣ መሰረት ትናንት ምሽት ሪያድ ገብተዋል።